ሀገራት በታሪካቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ትልልቅ ፈተናዎች የሚሻገሩባቸው ጊዜያት አሉ።
እነዚያ ጊዜያት ብዙውን ጊዜ በጦርነት ወይም በፖለቲካዊ ውጥረት የሚታወሱ ሳይሆን፣ ሕዝቦች ተቀምጠው ስለ ወደፊታቸው በሚመክሩበት ወቅት ነው።
ዛሬ ኢትዮጵያ በእንደዚህ ዓይነት ታሪካዊ መንገድ ላይ ቆማለች። ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም የሚካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከመደበኛ ውይይት በላይ ትርጉም ያለው ታሪካዊ ክስተት ነው።
ይህ ጉባኤ ስለ አንድ ወይም ሁለት ፖለቲካዊ ጉዳዮች ብቻ የሚወያይ አይደለም።
ስለ ኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያላቸውን ስምንት ግዙፍ አጀንዳዎች በማካተት የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ መሠረቶች እንደገና የሚፈትሽ ሂደት ነው።
የመጀመሪያ የሀገር ግንባታ አጀንዳ ሲሆን÷ ማንነት፣ የሀገር ባለቤትነት፣ የጋራ ሀገራዊ እሴቶች፣ የቋንቋ ጉዳዮች፣ ታሪክ እና ቅርስ የሚሉ ጉዳዮች በቀጥታ በምክክሩ ይታያሉ።
የሀገር ግንባታ ሂደት በኢኮኖሚ ልማት ብቻ አይለካም፤ ሁሉም ዜጎች "ይህች ሀገር የኔ ናት" ብለው እንዲሰማቸው የሚያደርግ የጋራ ማንነት መፍጠርን ይጠይቃል።
ሁለተኛው አጀንዳ የመንግሥት አደረጃጀትና የፖለቲካ ሥርዓት ሲሆን፣ ይህም በጣም ሰፊና ጥልቅ ከሆኑ የውይይት መስኮች አንዱ ነው።
የፌዴራል አወቃቀር፣ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት፣ የክልሎች ወሰን፣ የሀብት ክፍፍል፣ የምርጫ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት እና የህገ መንግሥት ትርጓሜ የሚመለከቱ ጉዳዮች በዚህ ስር ተካትተዋል።
ይህም ጉባኤው ስለ ኢትዮጵያ የወደፊት የፖለቲካ ሥርዓት መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመወያየት የሚያስችል መድረክ ማለት ነው።
የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ጉዳይ ደግሞ በብዙ ዓመታት ውስጥ ሲነሱ ከቆዩ ውስብስብ ጥያቄዎች መካከል ናቸው።
የከተሞቹ ህጋዊ አቋም፣ የውክልና ጉዳይ፣ ከክልሎች ጋር ያላቸው ግንኙነት፣ የቋንቋ አጠቃቀም እና የታሪካዊ ቅርሶች ጥበቃ የሚወያዩባቸው መሆኑ የጉባኤውን አጀንዳ ስፋት ያሳያል።
የሃይማኖት ጉዳዮች፣ ታሪካዊ ቅሬታዎች እና እርቅን የሚመለከቱ አጀንዳዎች ደግሞ ሌላው ትልቅ ምዕራፍ ናቸው።
ኢትዮጵያ ብዙ ሃይማኖቶችና ባህሎች የሚኖሩባት ሀገር በመሆኗ በሴኩላሪዝምና በሃይማኖት ነፃነት መካከል ያለው ሚዛን፣ ታሪካዊ ቅሬታዎችን የመፍታት መንገዶች፣ የእርቅ ሂደቶች እና በሃይማኖቶች መካከል ያለው መግባባት ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ናቸው።
የተቋማት ግንባታ፣ የህግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮች ደግሞ ሀገር በሰዎች ብቻ ሳይሆን፣ በጠንካራ ተቋማት እንደምትገነባ አመላካች ናቸው።
የፍትህ ተቋማት ነፃነት፣ የሚዲያ ገለልተኝነት፣ የሲቪል ማኅበራት ሚና፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ እና የዳያስፖራ ተሳትፎ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተካተቱ መሆናቸውም የምክክሩ አካታችነት ማሳያ ነው።
በተመሳሳይ መልኩ የመሬት ጉዳይ፣ የሀብት ክፍፍል፣ የሴቶች ጉዳይ፣ የወጣቶች ዕድል፣ የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ተጠቃሚነት፣ የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር እና አካታች ኢኮኖሚ የሚመለከቱ አጀንዳዎች የሚያሳዩት፣ ምክክሩ የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ዕለታዊ ኑሮ የሚነካ መሆኑን ነው።
እንዲሁም ሙስና፣ መልካም አስተዳደር እና ፍትሃዊ ፐብሊክ ሰርቪስ የሚመለከቱ ጉዳዮች ለሕዝብ በቀጥታ የሚሰማቸውን ችግሮች ወደ ምክክር ማምጣታቸውን ያሳያሉ።
የመንግሥት አገልግሎት በብቃት፣ በፍትህ እና በተጠያቂነት እንዴት ሊመራ ይገባል? የሚሉ ጥያቄዎችም ከዋና ዋናዎቹ ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።
ምናልባት ከሁሉም በላይ ተስፋ የሚጣልበት የሰላም ግንባታ አጀንዳ ነው። የግጭት መንስኤዎች፣ የተኩስ አቁም ሂደቶች፣ የሽግግር ፍትህ፣ የእርቅና ይቅርታ ሂደቶች፣ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች እና የሃይማኖት ተቋማት ሚና በዚህ ስር ተካትተዋል።
ይህም ጉባኤው ያለፈውን ለመረዳት ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት የማይደገም ሰላማዊ ሥርዓት ለመገንባት ጭምር ያለመ መሆኑን ያሳያል።
በመሆኑም ሐምሌ 8 የሚካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ተራ የውይይት መድረክ አይደለም። ኢትዮጵያ ስለ ታሪኳ፣ ስለ ማንነቷ፣ ስለ ፖለቲካዊ አወቃቀሯ፣ ስለ ኢኮኖሚያዊ ፍትህ፣ ስለ ሰላም እና ስለ ወደፊት አቅጣጫዋ በአንድ ጊዜ የምትመክርበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።
ይህም ከብዙ ዓመታት በኋላ ሰዎች ወደ ኋላ ተመልሰው “ኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ የከፈተችው በሐምሌ 8 ነበር” ብለው የሚያስታውሱበት ይሆናል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: