Search

የአንድነት ዐሻራ - ተፈጥሮን ለተፈጥሮ የመመለስ ታሪካዊ ጉዞ

ሰኞ ሰኔ 22, 2018 141

ምድር ሁላችንንም እኩል የምታኖር የጋራ ቤታችን ናት። የሰው ልጅ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በዕይታ እና በባህል ቢለያይም ሕይወትን ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ የጋራ አደራ ግን በአንድነት ያስተሣሥረዋል።

ኢትዮጵያውያን ዛሬ ልዩነቶቻቸውን ሁሉ ወደ ጎን ትተው፣ ለአንድ ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ እጆቻቸውን አበርትተው በጋራ እየተረባረቡ ይገኛሉ።

አሁን እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተፈጥሮ እንክብካቤ ብቻም ሳይሆን ትውልድን ታሳቢ ያደረገ የተስፋ መትከል ሕያው ውጥን ነው።

ቀደምት አባቶቻችን ለምለም መሬትን ጥቅጥቅ ያሉ አረንጓዴ ደኖችን እና ንጹህ አየር አስረክበውን አልፈዋል። በመሐል ግን ባለፉት ዘመናት ባለማስተዋል ተፈጥሮን ጎድተናል፣ ደኖችን መንጥረናል፣ ሕይወት የሚሰጡ የውኃ ምንጮችንም አድርቀናል።

አሁን ግን ያንን የታሪክ ስህተት ለማረም እና የተሸረሸረውን የምድር አካል ለመጠገን የምንረባረብበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።

ዛሬ የምናፈስሰው እያንዳንዱ ጠብታ ላብ እና የምንተክለው እያንዳንዱ ችግኝ፣ የትናንቱን ዕዳ ከፍለን ለነገው ትውልድ ለምለም ምድርን የምናወርስበት የተቀደሰ የይቅርታ እና የማካካሻ ጉዞ ነው።

ዛሬ በጋራ የምንተክላት አንዲት አነስተኛ ችግኝ፣ ነገ አድጋ ለብዙዎች ጥላ፣ ፍሬ እና መጠለያ የምትሆን የወደፊት ተስፋ ምልክት ናት።

ተፈጥሮን ለተፈጥሮ በመመለስ ምድራችንን ስናለማ፣ የነገው ትውልድ ከአየር ንብረት መዛባት ስጋት ነፃ ሆኖ በሰላም የሚኖርባትን ሀገር እየገነባን መሆኑን እናረጋግጣለን።

በአንድነት መንፈስ ተግባራዊ እየሆነ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ በጎርፍ እና በድርቅ ሳይሆን በልምላሜ እና በብልጽግና የምትጠቀስ ታላቅ ሀገር እንደሚያደርጋት ይታመናል።

ይህ የአንድነት ዐሻራ፣ ለምድር ያለንን ፍቅር በተግባር የምናሳይበት እና ለትውልድ የምንተወው ዘላቂ ሕያው ምስክር ነው።

በቴዎድሮስ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: