Search

የበጀት ዕቅዱ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማህበረሰብ ክፍል ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑ ተገለፀ

ማክሰኞ ሰኔ 23, 2018 61

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ29ኛ መደበኛ ስብሰባው በ2019 በጀት ዓመት የበጀት ዕቅድ ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል፡፡

የበጀት ዕቅዱና ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ  የ2019  በጀት ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማህበረስብ ክፍል ከግምት ውስጥ ያስገባና በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ኑሮ ውስጥ በጎ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የዜጎችን የመግዛት አቅም የሚያግዝና የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ማህበራዊ ወጪዎች የሚደረግ ድጎማን ከግምት ውስጥ በማስገባት  የተዘጋጀ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

አሁን ያለውን አገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከግምት ውስጥ ያስገባና ከዚህ ቀደም የነበሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶች ለማረም የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ያለን ትስስር የአገራችንን የፖሊሲ ነፃነት በጠበቀ መልኩ በቀጣይ ዓመታት ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ሚኒስትሩ ለኢኮኖሚያዊ መረጋጋት ፋይዳ በሌለውና ለህዝባችን ጥቅም በሌለው አጋርነት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት አይገባም ብለዋል፡፡

በቀጣይ ዓመታትም የታክስ መሰረቱን በማስፋት ከኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ጋር አብሮ የሚያድግ የበጀት አቅም ለመፍጠር እንደሚሰራም ነው የገለፁት፡፡

የ2019 ዓ.ም አጠቃላይ በጀት በትምህርት፣ በማህበራዊ ጉዳዮች፣ ለጤና፣ ለኢነርጂና መሰል ዘርፎች ትኩረት የሰጠ መሆኑን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡