Search

ኢትዮጵያ እና ሕንድ ቁልፍ በሆኑ ዘርፎች ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን በጥልቀት እያጠነከሩ ነው፡- አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ

ማክሰኞ ሰኔ 23, 2018 51

የኢትዮጵያ እና የሕንድ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በጤና አጠባበቅ፣ በግብርና፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)፣ በትምህርት፣ በአስተዳደር እና በመከላከያ ዘርፎች በጥልቀት እየተጠናከረ መሆኑን በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ገለጹ።

አምባሳደሩ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት፤ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የተደረሱ ታሪካዊ ስምምነቶችን በተግባር ላይ ለማዋል ቀጣይነት ያለው ሰፊ መሻሻል እየታየ ይገኛል።

ከእነዚህ ዋና ዋና ፕሮጀክቶች መካከል ሦስት ትላልቅ የሕንድ የጤና ጥበቃ አቅራቢዎች ጋር በመተባበር ልዩ ሆስፒታሎችን እና የዐይን ሕክምና ተቋማትን በኢትዮጵያ ለማቋቋም ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው።

እነዚህ ፕሮጀክቶች አሁን ላይ በላቀ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ እ.አ.አ ከ2026 ማብቂያ በፊት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ አክለውም፣ ኢትዮጵያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና በዲጂታል ጤና ላይ የምታደርገው እያደገ የመጣው ልዩ ትኩረት ለሁለቱ ሀገራት የጋራ ትብብር አዳዲስ ዕድሎችን የፈጠረ በመሆኑ፣ ይህም በቅርቡ ተጨባጭ ውጤት እንደሚያስገኝ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ሕንድ ከኢንቨስትመንት ባለፈ በአስተዳደርና በአቅም ግንባታ ረገድ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ በተለያዩ በስልጠናዎች አጠናክራ መቀጠሏ ተጠቅሷል።

በግብርናው ዘርፍም አምባሳደሩ ኢትዮጵያ በተለይ በስንዴ ምርታማነት እያስመዘገበች ያለችውን አስደናቂ ዕድገት አድንቀዋል።

ሕንድም ድርቅን መቋቋም በሚችሉ ሰብሎች፣ በመስኖ ቴክኖሎጂዎች እና በዘመናዊ የግብርና አሠራሮች ላይ ያላትን ሰፊ ልምድ በማካፈል የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና እና የግብርና ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደምትሠራ አስታውቀዋል።

በልዩ እሸቱ