የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡
ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ በምክር ቤቱ የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ በቋሚ ኮሚቴው የተዘጋጀውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
የፓሪሱን ስምምነት ጨምሮ ሀገራችን የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ውሎችና የገባቻቸውን የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳ ቃል ኪዳኖች ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚያግዝ አዋጅ ስለመሆኑ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
ሀራችን በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የምትጎዳ ሃገር እንደመሆኗ የካርበን ገበያ ስትራቴጂ ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ከፍተኛ ጥራት ላለው የአረንጓዴ ኢንቨስትመንት እና የቴክኖሎጂ ሸግግር ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር አስፈላጊ የሆነውን የህግ ማዕቀፍ እና ተቋማዊ አሰራር ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑም በውሳኔ ሀሳቡ ተገልጿል፡፡
አዋጁ ቀደም ሲል ያለበቂ የአሰራር ሥርዓት ሲተገበር የነበረው የግብይት ሂደት በግልፅ የህግ ማዕቀፍ እንዲመራ ለማድረግና ተበታትነው የነበሩ ደንብና መመሪያዎችን ወደ አንድ ወጥ የህግ ማዕቀፍ በማጠቃለል የአሰራር ወጥነት፤ ግልፅነት እና የአገልግሎት ቅልጥፍና ማስፈን የሚያስችል መሆኑን አቶ ደሳለኝ ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ አስገንዝበዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው አዋጁን አስፈላጊነት በስፋት ያነሱ ሲሆን፤ በኢትዮጵያን የካርበን ገበያ የህግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱ ለአረንጓዴ አሻራ ኢንቨስትመንት እንዲሁም ለቴክኖሎጂ ሽግግር ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።
በመጨረሻም ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ አዋጅ ቁጥር 1436/2018 ሆኖ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምዕ ጸድቋል።