አስፈላጊ የሆኑ አዋጆችና ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀት ኢትዮጵያ ከካርቦን ገበያ ተጠቃሚ እንድትሆን እየተሰራ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስዩም መኮንን ተናገሩ።
ትኩረትነቱ በካርቦን ገበያ ላይ ያደረገው ሁለተኛው የግብርና ሳይንስ ሴሚናርም በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትገኝ በጉባኤው ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ ሀገራችን ተግባራዊ ባደረገቻቸው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር፣ የታዳሽ ኃይል ልማት፣ የሌማት ትሩፋት እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አጠቃቀም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በምታደርገው ሂደት ውስጥ የአየር ንብረት ፋይናንስ ምንጮችን ማስፋት እንደሚገባ በመድረኩ ላይ ተነስቷል።
ለዚህም የካርቦን ገበያን በማጠናከር የአየር ንብረት የፋይናንስ ምንጭን ማሳደግ እንደሚገባ የገለጹት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስዩም መኮንን ይህንን የካርቦን ገበያ አሰራር በተገቢው መንገድ ለመምራትም አዋጅና ስትራቴጂዎች መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሰራቻቸው ስራዎች የሀገራችንን የደን ሽፋን እንዲጨምር፣ የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ እና የአፈር መሸርሸር እንዲቀንስ ማስቻል ተችሏል ብለዋል።
የካርቦን ግብይትም በዘርፉ ለሚሰማሩ አካላት ተጠቃሚነትን የሚያሳድግና ሂደቱን በተቀናጀ መልኩ ለመምራት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ስራ አስፈጻሚ ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መድረኩ በካርቦን ገበያ ላይ ያሉ ስራዎችን በጥናትና ምርምር ለመደገፍና ምሁራን በዘርፉ ያላቸውን አስተዋጽኦ ይበልጥ እንዲያሳድጉ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
በአባዲ ወይናይ