ታሪክ ራሱን በራሱ አያነብም፤ የሚተረጉመውና ሕያው የሚያደርገው ታላቅ ትውልድ ይሻል እንጂ። በኢትዮጵያ ምድር የተከማቹ የዘመን እዳዎችን ለማከም እና የታሪክን አዙሪት ለመቀየር ዘመኑን የዋጀው ትውልድ የመደመር ትውልድ ይባላል።
የመደመር ትውልድ ትልቁ መለያ እውነተኛ ሉዓላዊነትን ከፉከራና ቀረርቶ አውርዶ መሬት ላይ መትከሉ ነው። ሉዓላዊነት ዳር ድንበርን ከመጠበቅ ባለፈ፣ ሆድን በራስ አቅም መቻል፣ የተረጂነትን ካባ ማውለቅ መሆኑን በማመን፣ አስደናቂ የስንዴ ሉዓላዊነት ጉዞ ተጀምሯል። የግብርናውን ኋላ ቀርነት በመስበር፣ በኩታ ገጠም እርሻና በመስኖ ልማት ኢትዮጵያን ከስንዴ ለማኝነት በማላቀቅ በአፍሪካ ቀዳሚዋ የስንዴ አምራችና ላኪ እንድትሆን አስችሏታል። የሕዝብን የዕለት ጉርስ አብቃቅቶ ከማምረት አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉ፤ እጅግ አንጸባራቂ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችን ማሳያ ነው።
በተፈጥሮ ሉዓላዊነት መስክም ቢሆን፣ ሀገራችን ከመራቆት ወደ ልምላሜና አረንጓዴነት የምትሸጋገርበት አንጸባራቂ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተቀርጾ በተግባር ታይቷል። በአጭር ዓመታት ውስጥ ስድሳ አምስት ቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን ለመትከል፣ ርብርብ ላይ ስትሆን ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ልብሷን እንድትላበስና የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ መከላከያ ተምሳሌት እንድትሆን ተደርጓል።
በተጓዳኝም፣ የብርሃን ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ ከውኃ፣ ከፀሐይ፣ ከንፋስና ከከርሰ ምድር ሙቀት ንጹሕ ታዳሽ ኃይል (ኢነርጂ) የማመንጨት ታላቅ ራዕይ በተግባር እየተመነዘረ ይገኛል። የበርካታ ትውልዶች የናፍቆት እንባ የሆነውን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከነበረበት ውስብስብ ማነቆ አላቆ ማጠናቀቅ መቻሉ የመደመር መንግሥት ለብሔራዊ ኩራታችን የሰጠው ጽኑ አቋም ፍሬ ነው።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ፣ ኢትዮጵያ ራሷን እንድትችል አያሌ ምርቶችን፤ እንደ ምግብ ዘይት፣ አልሚ ምግቦች፣ የደንብ ልብሶችና መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ ጥገኝነት እንድንላቀቅ ተደርጓል። ማዕድናት "ከርሰ ምድር ነው" ተብለው በድቅድቅ ጨለማ ከሚተዉበት የታሪክ ምዕራፍ ወጥተው፣ የሀገርን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚያሳድጉ አዳዲስ ተግባራት ጋር ተቆራኝተዋል።
የሀገራችንን ዉብ ገጽታ ለዓለም በሚያስተዋውቀው የቱሪዝም ዘርፍም ቢሆን፣ "በገበታ ለሸገር"፣ "በገበታ ለሀገር" እና "በገበታ ለትውልድ" በሚሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ነባርና ድብቅ አቅማችንን አውጥተን በመጠቀም ለሀገር ገቢና ለሥራ ዕድል መፍጠሪያነት እያዋልናቸው ነው።
ይህ የመደመር መንግሥት ያመጣው ምናባዊ ከፍታ፣ በከተሞች ልማት በተለይም በዋና ከተማችን አዲስ አበባ ላይ ደምቆ ይታያል። የከተማ ኮሪደር ልማትን አምርሮ በመተግበር፣ አዲስ አበባ አሮጌ፣ ያረጀና የተዝረከረከ ገጽታዋን በፍጹም ጥላ፣ ጽዱ፣ አረንጓዴና የዜጎች ምቹ መኖሪያ እንድትሆን ተደርጓል። አዲስ አበባ ዛሬ የእውነተኛ ብልጽግና ተምሳሌትና የዘመናዊነት አፍሪካዊ መስተዋት ሆናለች። የተሰበረውን መንገድ ጠግኖ፣ የፈረሰውን መንደር በማደስ ዜጎች በሰውኛ ክብር እንዲኖሩ ማድረግ ትልቁ የሉዓላዊነትና የነፃነት ፊርማ ነው።
ከዚህ ሁሉ በላይ ግን፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ጂኦ-ፖለቲካዊ አቅም በማስከበር ረገድ የተወሰደው እጅግ ደፋርና ታሪካዊ እርምጃ የባሕር በር ጥያቄን በአደባባይ ማንሳቱ ነው። ከእልፍ ሚሊዮን በላይ ሕዝብና ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር ያለ ወደብ መቅረቷ የነበረንን የከረመ ስብራት ለመጠገን፣ የባሕር በር ጥያቄያችን ተገቢና ፍትሐዊ መሆኑን ዓለም በስፋት እንዲቀበለው ማድረጉ፣ የመደመር መንግሥት ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም ያለውን ጽኑ ዘብነት ያረጋግጣል።
በማጠቃለል፣ የመደመር መንግሥት ማለት የኢትዮጵያን መዋቅራዊ ችግሮች በተዋሰ ርዕዮተ ዓለም ሳይሆን በሀገር በቀል እውቀት፣ በገቢር ነበብነትና በፍጥነት የሚፈታ የዘመናችን የሥልጣኔ ሠረገላ ነው። በወርቃማው ፀሐይ ያጌጡት የስንዴ ማሳዎቻችን፣ ያንሰራሩት ውብ ከተሞቻችን፣ የገነባናቸው ሰማይ ጠቀስ ግድቦችና ያቆጠቆጡት ደኖቻችን፤ ሁሉም በአንድ ድምፅ የሚመሰክሩት አንድ አይነኬ ሐቅ አለ፡- ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን በጠንካራ የልማት መሠረት ላይ ያቆመች፣ ሩቅ አላሚ የመደመር መንግሥት አግኝታለች!
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ