ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ፣ ኢትዮጵያ የነፃነት ተምሳሌት፣ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት፣ እና የብዙ ፀጋዎች ማህደር ሆና እናገኛታለን።
አባቶቻችን በደማቸው አቅንተውና ጠብቀው ያቆዩልንን ይህች ምድር፣ ሀብቷ ሳይደመርና አ ቅሟ ሳይቀናጅ ለዘመናት በመቆየቱ ምክንያት፣ በእጦት አዙሪትና በድህነት ማጥ ውስጥ ስትዳክር ኖራለች።
“የኢትዮጵያውያንን ህይወት እንለውጣለን” የሚለው መፈክር በተፈራረቁ መንግስታትና ትውልዶች ዘንድ በተደጋግሚ ቢነገርም፣ በተግባር ግን እንደ ጉም ርቆን፣ እንደ ህልም ተንሳፎ ቆይቷል።
ዘመናት ነጎዱ፣ ትውልዶች ተፈራረቁ፤ እኛ ግን በተረገጥንበት ቦታ መቆማችንን አልተውንም። በዚህ የታሪክ መስቀለኛ መንገድ እና በተከማቸ የቤት ስራ አጣብቂኝ ውስጥ ነው እንግዲህ "የመደመር መንግስት" ብቅ ያለው።
ለመሆኑ የመደመር መንግስት ምንነት ምንድን ነው?
የመደመር መንግስት ማለት መከፋፈልን፣ መነጠልን፣ እና የአንዱን መቃብር የሌላው ዙፋን የሚያደርገውን የዜሮ ድምር ጨዋታ በመፀየፍ፣ ሀገራዊ ፀጋዎችንና አቅሞችን ወደ አንድ የብልፅግና ወንዝ የሚያፈስ ስርዓት ነው። በመደመር ፍልስፍና መነፅር፣ የመንግስት ሚና እንደ ባለፈው ዘመን ሁሉን አድራጊ ፈጣሪ ወይም ጨቋኝ መሆን ሳይሆን፣ የትብብር ሞተር መሆን ነው።
ይህ መንግስት ዜጎችን፣ የግሉን ዘርፍ፣ እና ሀገራዊ አቅሞችን በማስተባበር፤ ትላንት ያመለጠንን የባከነ ጊዜ "በፈጠራ እና በፍጥነት" የሚያካክስ፣ ገቢር ነበብ (Pragmatic) የሆነ የዘመነ መንግስታዊ መዋቅር ነው።
መሰረታዊ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ዲፓርቸሩም ይሄው ነው፡ ትናንትን ከስህተቱ ተምሮ ማረም፣ ዛሬን በትጋት መስራት፣ እና ነገን በምናብ ተልሞ ማለም።
የመደመር መንግሥት ስንል፣ በፍልስፍና መሠረቱ ከታሕታይ መዋቅር (እንደ ኢኮኖሚ እና መሠረተ ልማት) ለውጥ ይልቅ ለላዕላይ መዋቅር (አስተሳሰብ እና ባህል) ለውጥ ቅድሚያ የሚሰጥ ሥርዓት ማለታችን ነው። ይህ መንግሥት የማኅበረሰብን ልዩ ልዩ ጸጋዎች፣ ዕሴቶች፣ እና አቅሞች ማሰባሰብ ለብልጽግና ወሳኝ መሆኑን በፅኑ ያምናል።
የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ኃይሎች በሚፈጥሩት ፍትጊያ ውስጥ ሚዛን (ወርቃማውን አማካይ) በመጠበቅ ሁሉንም አቅፎ የሚጓዝ ነው።
ይህንን እውነት ይበልጥ ለመረዳት የመደመርን መንግሥት መሠረታዊ መለያዎች ካለፉት መንግሥታት ታሪክ ጋር ማነፃፀር ግድ ይላል።
የሀገራችን የፖለቲካ ጉዞ ከውጭ ሀገር (ከምዕራብም ሆነ ከምሥራቅ) የልማት ሞዴሎችን እንዳለ ገልብጦ በማምጣት የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነታ ለማሳጣት ሲጥር የኖረ ፤የንጉሡ ሥርዓት "ሰማይ አይታረስ፣ ንጉሥ አይከሰስ" በሚል መርህ አይነኬነትን ያነገሠ፣ ለውጥን የሚጠላና ቆሞ-ቀርነትን ያተረፈ ፊውዳላዊ ሥርዓት ሆና የተካው የደርግ መንግሥት ደግሞ የሶቪየትን ሞዴል በጭፍን በመከተል "ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ" እንዲሉ፣ በኅብረተሰብአዊነት ስም የግሉን ዘርፍ አቀጭጮ፣ ሀብት ፈጣሪነትን አውግዞ ሀገርን ለከፋ የኢኮኖሚ ቀውስና አዙሪት ዳርጓል።
የኢሕአዴግ መንግሥት በበኩሉ ብሔርን ከአስተዳደራዊ ወሰን ጋር በማስተሳሰሩ ጽንፈኝነትን ያቀጣጠለ፣ ሀገራዊ አንድነትን የሸረሸረ እና በመጨረሻም የሀገር ሀብት በጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን እጅ እንዲወድቅ ያደረገ ፣እነዚህ ሁሉ መንግሥታት ከዜሮ ድምር ፖለቲካ፣ ተቀናቃኝን አሳዶ ከማጥፋት፣ እና የሕዝብን እያደገ የሚመጣ ፍላጎት በጊዜው ካለመመለስ አባዜ አልወጡም ነበር።
ከዚህ በተቃራኒ፣ የመደመር መንግሥት የገበያ መር እና የመንግሥት መር ፅንፎችን በማስወገድ "የትብብር ሞዴልን" ገንዘቡ ያደርጋል። የግሉ ዘርፍ ሀብት እንዲፈጥር ሲያበረታታ፣ መንግሥትም ራሱ በኢንተርፕረነርሺፕ (ስራ ፈጣሪነት)ዕሳቤ አዳዲስ ዘርፎችን በመፍጠርና ሀገራዊ ሀብትን በማከማቸት ይተጋል።
የመደመር መንግሥት ሌላው ግዙፍ መለያው "የዔሊ ጉዞን" ሰብሮ በ"ፍጥነት፣ ፈጠራ እና ዝላይ" መገስገሱ ነው። አዳጊ ሀገራት የበለፀጉት ሀገራት የሄዱበትን የክፍለ ዘመናት አዝጋሚ (ደረጃ በደረጃ) ጉዞ መከተል የለባቸውም በማለት፣ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በቀጥታ በመቀላቀል "የዝላይ መንገድን" (Leapfrogging) በመጠቀም ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ለማድረግ ይሠራል።
ከዚህም ባሻገር፣ የመደመር መንግሥት "ምናባዊ ከፍታን" ተላብሷል። የይድረስ ይድረስ ጊዜያዊ ማስታገሻዎችን ትቶ፣ እንደ አዲስ አበባ ወንዞች ልማት (ገበታ ለሸገር) እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሮችን በመሰሉ ሩቅ አላሚ ፕሮጀክቶች ሀሳብን ወደ መሬት በማውረድ "የማድረግ ዐቅሙን" በተግባር አረጋግጧል።
በአጠቃላይ የመደመር መንግሥት የትናንትናውን የተከማቸ ዕዳ በፈጠራ የሚያቃልል፣ ያመለጠንን የኢንዱስትሪ አብዮት ጊዜ የሚያካክስ፣ እና ኢትዮጵያን በጠንካራ ሥርዓታዊ መዋቅርና ትብብር ወደ ብልጽግና ማማ የሚያሸጋግር መሪ ብርሃን ነው።
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ