Search

“በጎነት ከባዕዳን ጥገኝነት አውጥቶ ወደ ክብራችን የመለሰን የኢትዮጵያዊነት እሴት ነው”፦ ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ማክሰኞ ሰኔ 23, 2018 46

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በጎነት ሀገራችንን ከባዕዳን ተመጽዋችነት አውጥቶ ወደ ነባር ክብራችን የመለሰን ታላቅ የኢትዮጵያዊነት እሴት መሆኑን አስታውቀዋል።

ከንቲባዋ ኢትዮጵያ ከመከባበርና ከመደጋገፍ የሚቀዱ በርካታ እሴቶች ያሏት የባለብዙ ማንነትና ባህል ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት ለነዚህ የኖሩ የመረዳዳት ባህሎች በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ እሴቶቹ ደብዝዘው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

እንደ ደቦ፣ እድር እና እቁብ የመሳሰሉ የደለቡ ወረቶች ባለቤት ብንሆንም፣ እነዚህን ጥልቅ እሴቶች ወደ ጎን በመተው የባዕድን እጅ በመጠበቅ ስንቦዝን ቆይተናል ብለዋል።

ቀድሞ በአዲስ አበባ አንድ ሰፈር ላይ አነስተኛ የሕዝብ መጸዳጃ ቤት ለመገንባት እንኳ ከውጭ እርዳታ መለመን የተለመደ ተግባር የነበረ ሲሆን፣ ይህ ዘመናዊ ልመናም የሀገሬው ሕዝብ ተረጂነትንና ጠባቂነትን አምኖ እንዲቀበል አድርጎት እንደነበር አብራርተዋል።

ከለውጡ በኋላ ግን ይህንን አሉታዊ አመለካከት በመገልበጥ ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ መሸጋገር መቻሉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አብራርተዋል።

መሪዎች የረሳነውን የመረዳዳት ባህል ለመመለስ በሠሩት ሕዝብን የማስተባበር ሥራ፣ ወደ ውስጣችን ተመልክተን ያለንን ዕምቅ አቅም መገንዘብ ችለናል።

በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ባለፉት ዓመታት የዘመሙ ጎጆዎችን በማቃናት እንደ ልደታ፣ ለሚ፣ እና ላፍቶ የመሳሰሉ ታላላቅ የበጎነት መንደሮች በአዲስ ገጽታ ተገንብተው ተመርቀዋል።

በነዚህ ዓመታት በበጎ ፈቃድ የቤት እድሳትና ግንባታ መርሐ-ግብር 46 ሺህ 400 ቤቶች ሲገነቡ፣ 90 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል፣ በርካታ ዜጎች ከጎዳና ተነስተዋል፣ እንዲሁም አቅመ ደካሞች ነፃ የሕክምና አገልግሎት አግኝተዋል።

ያረጁና ለከተማዋ ገጽታ የማይመቹ ሰፈሮችን በመለወጥ የአዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከፍ ያደረጉ በርካታ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ በሕዝቡ በጉልበት፣ በዕውቀትና በገንዘብ የተደረገው የነዚህ በጎ ተግባራት አስተዋጽኦ ሲሰላ 55.7 ቢሊዮን ብር መድረሱን ከንቲባዋ ጠቁመው፣ ይህ ሕዝብ ከተባበረ ምንም ማድረግ እንደማይሳነው ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።

ይህንኑ አስደናቂ የበጎነት ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል፣ ዘንድሮም አዳዲስና ትኩረት የሚስቡ ግዙፍ ፕሮግራሞች በቅርቡ ይፋ ተደርገው ወደ ሥራ መገባቱን ከንቲባዋ አብስረዋል።

በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 16 የተለያዩ ፕሮግራሞች የተነደፉ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል በዋናነት 2 ሺህ 500 አዳዲስ ቤቶችን በመገንባት 12 ሺህ 500 አቅመ ደካማ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ውጥን ተይዞ ትግበራ ተጀምሯል።

በተጨማሪም 6 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ከተማ አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር የተጀመረ ሲሆን፣ አዲስ አበባን ውብና ጽዱ ለማድረግ ታላቅ የክረምት የጽዳት ዘመቻ ንቅናቄም እየተካሄደ ይገኛል።

ከዚህ ጎን ለጎን የከተማዋን ወንዞች ተፈጥሯዊ ፍሰት በመጠበቅ የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የሚያስችሉ የግንባታና የቦይ ማጽዳት ሥራዎች በከፍተኛ ደረጃ እየተከናወኑ ነው።

ዜጎች እስከ ደም ልገሳ በሚደርስ መስዋዕትነት፣ በዕውቀታቸውና በጉልበታቸው ሀገራቸውን የሚያገለግሉበት ይህ የተቀደሰ የበጎነት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አረጋግጠዋል።