ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ የኤምባሲዎች እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች በእንጦጦ ፓርክ የአረንጓዴ ዐሻራቸውን አኖሩ።
ይህ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን በጋራ ያዘጋጁት ነው።
የበርካታ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ ላይ ቀጥታ መሳተፋቸው፣ ሥራው ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
የአምባሳደሮች፣ የዲፕሎማቶች እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች በአረንጓዴ ዐሻራ መሳተፋቸው ኢትዮጵያ ለዘርፉ አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ እንድታገኝና ትኩረት እንዲሰጣት እንደሚያስችል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ ተናግረዋል።
በተጨማሪም መርሐ ግብሩ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል።
በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፉት ዲፕሎማቶች በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ዓለም በአየር ንብረት መዛባት እየተፈተነች ባለበት ወቅት እየተከናወነ በመሆኑ ወቅቱን የጠበቀና አስፈላጊ ተግባር ነው ብለዋል።
ይህ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ ለሌሎች ሀገራትም አርዓያ የሚሆንና ተመራጭ ተሞክሮን የሚያሰፋ መሆኑን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።
በአስማረ ብርሃኑ