ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪካዊ ተፈጥሯዊና የባህል ቅርሶች ማህደር ብትሆንም ይህን ዕምቅ ፀጋ ወደ ሀገር ከፍታና ብልፅግና ቀይራ መጠቀም ሳትችል ዘመናት ተቆጥረዋል።
ሆኖም በምናብ ከፍታ ነገን አሻግሮ በመመልከት ቃልን በተግባር የመኖር ባህልን በተቋማዊ መሰረት የገነባው የመደመር እሳቤ የቱሪዝም ዘርፉን የሀገር ምሰሶ አድርጎ ተነስቷል።
የመደመር ፍልስፍና ዳራው ትናንትን ከነክብሩ ጠብቆ፣ የተበታተኑ ሀገራዊ ፀጋዎቻችንን በማሰባሰብና እሴትን በመጨመር ወደ ላቀ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም መቀየር ነው።
በዚህም መነሻነት የመደመር መንግሥት አዲስ አበባን ከጥልቅ ጉስቁልና በማውጣት ወደ ሚመጥናት የውበት ከፍታ እያሸጋገራት ይገኛል።
ይህ ጥረት በዋና ከተማዋ ብቻ ሳይገደብ ላለፉት አምስት ዓመታት በመላ የሀገራችን ክፍሎች የተመዘገቡት ስኬቶች የዚህን ዕሳቤ ጥልቀትና ተግባራዊነት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።
ሀገራችን ለዘመናት ተዘንግተውና አቧራ ጠጥተው የቆዩ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶቿን ደረጃቸውን በጠበቀና በጥናት ላይ በመመስረት በማደስና በመንከባከብ በቱሪዝም ዘርፍ አስደናቂ ውጤት አስመዝግባለች።
ታሪካዊ ገፅታቸውን ሳያጡ በዘመናዊ አቀራረብ ሕይወት ዘርተው ከተነሱት ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን፣ የሐረር ጀጎል ግንብን፣ የጎንደር አብያተ መንግሥታትን፣ የጅማ አባ ጅፋር ቤተ መንግሥትንና የሶፍ ኡመር ዋሻን ጨምሮ በርካታ ድንቅ ቅርሶች ይገኙበታል።
የእነዚህ የቅርስ ዕድሳት ፕሮጀክቶች ፋይዳ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማስፋትና ማራኪ ከማድረግም በእጅጉ የዘለለ ነው።
በዘርፉ አዲስ መነቃቃትን በመፍጠር የግሉ ዘርፍ በኢንቨስትመንት በስፋት እንዲሳተፍና ተወዳዳሪነቱ እንዲጠናከር ምቹ መደላድል ፈጥረዋል።
አዳዲስ የቱሪዝም ማዕከላት መበራከታቸው የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ከማራዘሙም ባሻገር ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬና አጠቃላይ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ አስችሏል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነትና የቅርብ ክትትል የተተገበሩት እነዚህ የቅርስ ልማትና ጥበቃ ስራዎች የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር አድርገዋል።
መንግሥት በቅርስ ጥበቃና ልማት ላይ የፈጠረው ይህ አዲስ ዕይታ የሀገራችንን የካበተ የታሪክ ሃብት በአግባቡ ጠብቆ ወደ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መቀየር እንደሚቻል አረጋግጧል።
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ