Search

መኖሪያ ቤታቸውን የህዝብ ቤተ-መጻሕፍት ያደረጉት አዛውንት

ማክሰኞ ሰኔ 23, 2018 57

የንባብ ባህል ማደግ የግለሰቦችን ስብዕና ከማነፅ ጀምሮ አገር በመገንባት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ኢትዮጵያ ያልታዩና ያልተነገሩ በርካታ ታሪኮች እንዳሏት ቢታወቅም፤ የዜጎቿ የንባብ ባህል ግን የታሪኳን ያህል አለማደጉ ይነገራል። ለዚህ ደግሞ ዘመኑ የፈጠረው የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ፣ የመጻሕፍት ዋጋ መናር እንዲሁም በቂና ምቹ የቤተ-መጻሕፍት አለመኖር በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ታዲያ የንባብ ባሕልን ለማዳበርና ምክንያታዊ ትውልድ ለመፍጠር የንባብ ማዕከላትን ከማስፋፋት ጀምሮ አስፈላጊውን ግብዓት ማሟላት ለነገ የማይባል ተግባር ነው።

ያነበበና ያወቀ ትውልድ የመፍጠር ኃላፊነት ከመንግሥት ባሻገር የረድኤት ድርጅቶችና የሌሎች በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ሚና የጎላ መሆኑን በተግባር ያሳዩ አንድ አዛውንት በባሕር ዳር ከተማ ይገኛሉ።

እኚህ በጎ ፈቃደኛ የ74 ዓመቱ አዛውንትና ጡረተኛው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ አቶ ሕሩይ ደመላሽ ናቸው። ግለሰቡ አገራቸውን ለ37 ዓመታት በተለያዩ የሙያ መስኮች በታማኝነት ያገለገሉ ሲሆን፤ በጡረታ ከተሰናበቱበት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በመኖሪያ ቤታቸው መለስተኛ ቤተ-መጻሕፍት በመክፈት ለአካባቢው ማኅበረሰብ ነፃ የንባብ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

ከ20 ዓመታቸው ጀምሮ መጻሕፍትን መግዛትና ማንበብ የጀመሩት አቶ ሕሩይ፤ "ንባብ ለሕይወቴ መሠረት፣ ከሰዎች ጋር መግባቢያ፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዬን የምመለከትበት እንዲሁም ማኅበረሰቡን በጥልቀት የማውቅበት መነጽሬ ነው" ይላሉ።

አዛውንቱ ባለፉት 50 ዓመታት በትጋት የሰበሰቧቸውን ከ2,530 በላይ መጻሕፍት በመኖሪያ ቤታቸው ቅጥር ግቢ ባዘጋጁት መለስተኛ ቤተ-መጻሕፍት ውስጥ ለንባብ በማብቃት ለአንባቢያን አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው።

ሳይንሳዊ፣ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ መጻሕፍትን በዕድሜ ዘመናቸው መሰብሰብ የቻሉት አቶ ሕሩይ፤ ለባሕር ዳር ከተማና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ያለምንም ክፍያ መጻሕፍትን በውሰት በመስጠት ትውልዱ እንዲያውቅና እንዲያነብ በማድረግ የዜግነት ድርሻቸውን በከፍተኛ ኃላፊነት እየተወጡ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅትም በርካታ መደበኛ አንባቢ ደንበኞችን ማፍራት እንደቻሉ ተናግረዋል።

አሁን ላይ የንባብ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን የሚጠቁሙት አቶ ሕሩይ፤ ለዚህም ማኅበራዊ ሚዲያ፣ የመጻሕፍት ዋጋ መናርና የምቹ ቦታዎች እጥረት ተግዳሮት መሆናቸውን ያነሳሉ።

ትውልዱ ከስሜት የፀዳና ምክንያታዊ መሆን ይኖርበታል ያሉት አዛውንቱ፤ የንባብ ባሕልን ለማዳበር ከግለሰቦች ጀምሮ ማኅበረሰቡ፣ ረድኤት ድርጅቶችና መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተስፋሁን ደስታ