Search

አዲስ ሐሳብ፣ አዲስ አካሄድ እና አዲስ ትውልድ ለጠንካራ ሀገር

ማክሰኞ ሰኔ 23, 2018 54

የመደመር እሳቤ በባሕርዩ ተነጣጣይ የነበሩ ሀገራዊ አቅሞችንና ትርክቶች ወደ አንድ ማዕከላዊ የስበት ማዕከል በማምጣት አዲስና ሁለንተናዊ ሀገረ-መንግሥት የመገንባት ስትራቴጂካዊ ፍልስፍና ነው።

ይህ እሳቤ የኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ጉዳይ ሲያነሳ ልዩነቶችን አጥፍቶ ወደ አንድ ወጥ ሥርዓት የመግባት ዝንባሌን በጽኑ ይቃወማል።

ይልቁንም ብዝኃነትን የሀገር ውበትና የጥንካሬ ምንጭ አድርጎ በመውሰድ እነዚህን የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በጋራ ሀገራዊ ራዕይ ሥር የሚያስተሳስር ነዉ፡፡

በዘመናዊው ዓለም አውድ ሀገራዊ ስኬትን ማረጋገጥ የሚቻለው ከተበታተነ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አካሄድ ወጥቶ ልዩነቶችን ወደ ሚደጋገፍና ወደሚቀናጅ የጋራ ኃይል ማሳደግ ሲቻል ብቻ ነው።

ይህን ከውህደት ወደ ስኬት የሚደረግ ጉዞ በጥልቀት ስንመለከተዉ የመደመር ፍልስፍና በውስጡ ሦስት መሠረታዊ ምሰሶዎችን ይዟል፤ እነሱም ያለፈውን ስኬት ማስቀጠል፣ ስህተቶችን ማረም እና የወደፊት ተስፋዎችን ማቅረብ ናቸው።

ይህፍ ልስፍና  በኅብረ-ብሔራዊት ሀገር ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ብሔሮች፣ ቋንቋዎችና ባህሎች እንደ ስጋት ከመቁጠር ይልቅ፣ እርስ በርሳቸው ሲደመሩና ሲቀናጁ የላቀ ሀገራዊ አቅም እንደሚፈጥሩ በምክንያት ያስረዳል።

በተናጠል የሚደረግ የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ጉዞ የሚያስገኘው ውጤት ውስንና ለትንኮሳዎች ተጋላጭ መሆኑን ታሪክ አሳይቶናል። በአንጻሩ፣ ብዘኃነትን ያቀፈ ስልታዊ ውህደት ሲፈጠር ግን እያንዳንዱ አካል የራሱን ማንነት ይዞ ከሀገራዊ ማንነት ጋር በሰላማዊ መንገድ እንዲተሳሰር ያደርገዋል።

ከፖለቲካዊ ኢኮኖሚ አንጻር ስንገመግመው፣ መደመር የሀብትና የዕድል ክፍፍልን ፍትሐዊ በማድረግ የኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ማኅበራዊ መሠረት ያጠናክራል።

በአንድ ሀገር ውስጥ የሚታዩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች፣ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሮች በተናጠል ጥረት ሊሳኩ አይችሉም። እነዚህን ሁሉን አቀፍ ስኬቶች ዕውን ለማድረግ የዜጎችና የብሄር ብሔረሰቦች የጋራ ተሳትፎና የአዕምሮ ውህደት የግድ ይላል።

የ"መደመር" ዋናው ስኬትም ይኸው ነው፤ ሕዝቡን ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካና ከማኅበራዊ ዘርፎች እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ አካታች ሥርዓት በመዘርጋት፣ የጋራ ባለቤትነት ስሜትን ይፈጥራል።

ይህ የባለቤትነት ስሜት ደግሞ በተራው ለሀገራዊ መግባባትና ለዘላቂ ሰላም ዋነኛው ዋስትና ይሆናል።

ይሁን እንጂ ይህ የኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ጉዞ ያለ ተግዳሮት የሚጓዝ አይደለም። ነጠላ ትርክት ፣ የራሴ ብቻ ይቅደም ዝንባሌዎችና ታሪካዊ ቅሬታዎችን ለፖለቲካ ፍጆታ የመጠቀም አባዜዎች የኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ጉዞውን በየጊዜው የሚፈትኑ ዋና ዋና ማነቆዎች ናቸው። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የመደመር እሳቤ እንደ መፍትሔ አቅጣጫ የሚመጣው።

ፍልስፍናው ከሁከትና ከብጥብጥ ይልቅ በሐሳብ ልዕልና፣ በሀገራዊ ምክክርና ለድርድር ዕድል በመስጠት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ባህልን ያበረታታል። ይህም ማለት ልዩነቶችን በኃይል ለመጫን ከመሞከር ይልቅ፣ በውይይትና በመተማመን መድረኮች አማካኝነት የጋራ መጋጠሚያ ነጥቦችን ማብዛት ላይ ያተኩራል።

ስለሆነም በመደመር እሳቤ ላይ የተገነባ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ጊዜያዊ ስምምነት ሳይሆን ስልታዊና መዋቅራዊ የሀገር ግንባታ ሂደት ነው።ይህ ሂደት አዲስ ሐሳብን፣ አዲስ አካሄድንና አዲስ ትውልድን የሚያካትት በመሆኑ ኢትዮጵያን ካለችበት ውስብስብ ተግዳሮት አውጥቶ ወደ ላቀ የብልጽግና ምዕራፍ ያሸጋግራታል።

ግለሰቦች፣ ማኅበረሰቦችና ብሔረሰቦች በተናጠል ከሚያመጡት ስኬት ይልቅ ተደምረውና ተቀናጅተው የሚፈጥሩት ሀገራዊ ኃይል እጅግ የላቀና የማይበገር መሆኑን መገንዘብ የነገዋን ጠንካራ አገር ለመገንባት ብቸኛውና ዘላቂው መንገድ ነው፡፡

በረከት ሽመልስ