የአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት መለኪያ ለዜጎች የሚሰጠው የአገልግሎት ፍጥነት፣ ግልጽነትና ጥራት መሆኑ በሚታመንበት በዚህ ወቅት፤ "አዲስ መሶብ" የዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት በኢትዮጵያ የአገልግሎት አሰጣጥ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሆኗል።
ይህ የአገልግሎት አሰጣጥ ዜጎች ከተለያዩ ተቋማት የሚፈልጓቸውን በርካታ አገልግሎቶች ከመታወቂያና ፓስፖርት ዕድሳት ጀምሮ እስከ ንግድ ፈቃድና የግብር ክፍያ በአንድ ማዕከል በተቀናጀ የዲጂታል አሠራር በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ እያስቻለ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን ዘመናዊ አገልግሎት ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል እኩል ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ጥረት እያደረገ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ለሕዝብ ክፍት የተደረጉት የአዲስ መሶብ ቅርንጫፍ ማዕከላት፣ ሕብረተሰቡ ብዙም ሳይርቅ በአቅራቢያው ጉዳዩን እንዲያስፈጽም አስችለውታል።
ይህም ዜጎች ለጉዳይ ማስፈጸሚያ ያጠፉት የነበረውን ጊዜ፣ ገንዘብና እንግልት በእጅጉ የቀነሰ ሲሆን፤ የሚሰጡት አገልግሎቶችም በአንድ የተወሰነ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ የማይገደቡ፣ ይልቁንም እርስ በእርስ የተናበቡና የተቀናጁ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡
ተገልጋዮችም በየትኛውም አቅራቢያቸው በሚገኝ የመሶብ ማዕከል በመሄድ ጊዜና ጉልበትን ከብክነት በታደገ መልኩ ሁሉንም ዓይነት አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ አድርጓል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ማዕከሉ በከፍተኛ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት የተደራጀ በመሆኑ አሠራሩን ሙሉ በሙሉ ከሌብነትና ከብልሹ አሠራር የጸዳ ከማድረጉም በላይ፤ ዜጎች ቀደም ሲል በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይገጥማቸው የነበረውን መጉላላትና የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በዘላቂነት ለመቅረፍ አስችሏል።
ከአገልግሎት ጥራቱ ባሻገር ማዕከላቱ ምቹ የሥራ ከባቢ የተፈጠረላቸውና የሕፃናት ማቆያን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች የተሟሉላቸው ሲሆን፤ የሥራ ሂደቱም በሰለጠኑ አዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንና በነባር ሠራተኞች ውህደት የሚመራ በመሆኑ ለመፃኢው የአገራችን የአገልግሎት አሰጣጥ መዘመን ብሩህ ተስፋን የሰነቀ ሆኗል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአሁኑ ወቅትም የአዲስ መሶብ ማዕከላትን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሳደግ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ አበክሮ እየተሠራ ይገኛል።
በብሌን ደምበሎ