የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ታሪክን ከዘመናዊ የከተማ ፕላን ጋር በማቀናጀት የጀመረው የወንዞች ዳርቻ ልማት የነዋሪዎችን ማኅበራዊ ኑሮ ከማቃለል ባሻገር የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር እና የከተማዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።
የዚህ ታላቅ ስኬት ማሳያ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት የተደረገው የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የመዲናዋን የቱሪስት መዳረሻነት በማስፋት ረገድ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
መነሻውን ከመዲናዋ ሰሜናዊ አቅጣጫ አድርጎ አዲስ አበባን ከፍሎ የሚፈሰው የቀበና ወንዝ የመጀመሪያው የመንገድ ድልድይ የተገነባለት ቀዳሚ ታሪካዊ ስፍራ ቢሆንም፣ ለበርካታ ዓመታት ግን ትኩረት የተነፈገው በመሆኑ ለከፍተኛ ብክለት፣ ለሕገ-ወጥ ግንባታ፣ ለአፈር መሸርሸር እንዲሁም በክረምት ወቅት ለጎርፍና ለጸጥታ ሥጋት ምንጭ ነበር።
በአሁኑ ወቅት በተተገበረው አጠቃላይ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ግንባታ ይህ ቀደም ሲል የነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ ተቀይሮ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ ማራኪና ሳቢ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራ ለመሆን በቅቷል።
በከተማዋ በአጠቃላይ 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 87 ነጥብ 6 ሄክታር መሬት የሸፈነው ይህ ፕሮጀክት ከተፈጥሮ ጋር በተስማማ እና በዘላቂ ልማት እሳቤ የተገነባ ነው። በወንዙ ዳርቻ የተገነቡት ዘመናዊ የመከላከያ ግንቦች የአካባቢውን የጎርፍ ሥጋት ሙሉ በሙሉ ያስቀሩ ሲሆን፣ የተተከሉ ጥቅጥቅ ያሉ ዛፎች አረንጓዴነትን በማሻሻል ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።
ከከተማዋ ውበትና ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር ይህ ፕሮጀክት ለአካል ብቃት እንቅስቃሴና ለእግር ጉዞ የሚሆኑ ውብ መንገዶችን፣ የብስክሌት መስመሮችን፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ድልድዮችን፣ ዘመናዊ ቤተ-መጻሕፍትን፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን፣ ሰፋፊ ፕላዛዎችን፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎችንና የሕፃናት መጫወቻዎችን ባካተተ አግባብ የተገነባ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተጨማሪም ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ)፣ ንጹሕ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች፣ መለስተኛ ግድቦች፣ ሰው ሠራሽ ፏፏቴዎች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የኪነ-ጥበብ መድረኮችና በርካታ የንግድ ሱቆችን እንዲይዝ ተደርጓል።
በዚሁ መርሐ-ግብር የተገነቡ ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶችና የንግድ ማዕከላት ለአካባቢው ነዋሪዎችና ለወጣቶች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ሆነዋል።
አዲስ አበባ ታሪክንና ተፈጥሮን በማጣመር እያካሄደች ያለችው የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራ እጅግ ተስፋ ሰጪ በመሆኑ፣ መዲናዋን በአፍሪካና በቀጣናው ተመራጭ የኢኮኖሚ፣ የሕዝብ ጤና እና የዓለም አቀፍ ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ለማስቻል ተደማሪ አቅሞችን በማሰባሰብ በአንድነት መሥራት ከሁሉም ይጠበቃል።
በብሌን ደንበሎ