(የዕለቱ መልዕክት)
ኢትዮጵያ በታሪኳ አዲስ እና ስልታዊ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። ይህ ምዕራፍ የተፈጥሮ ጸጋዎችን በኩራት ከመቁጠር እና ከመቀኘት ባለፈ እነዚያን እምቅ ሀብቶች ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ እና የጂኦፖለቲካ አቅም በመለወጥ ሀገራዊ ልዕልናን ለማረጋገጥ የሚደረግ የታሪክ መታጠፊያ ነው።
ለረጅም ዘመናት በድህነት፣ በዕርዳታ ጥገኝነት እና በውስጥ ስጋቶች ታጥሮ የቆየው የቀድሞው ዲፕሎማሲ ዛሬ በተግባር ተረትቷል። በምትኩም ቀጣናዊ ትሥሥርን የሉዓላዊነት እና የአህጉራዊ መሪነት ማረጋገጫ ያደረገው የመደመር መንግሥት ስልታዊ ራዕይ በተጨባጭ መሬት እየረገጠ ይገኛል።
በተለይም የታዳሽ ኃይል ሀብትን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዋና ምሰሶ አድርጎ የመጠቀም ስትራቴጂ፣ የሀገርን የፖለቲካ ተጽዕኖ እና "ለስላሳ ኃይል" (Soft Power) ከፍ ወዳለ ማዕረግ እያሸጋገረው ነው።
ኃይል ለአዳዲስ የቴክኖሎጂ አብዮቶች፣ ለዲጂታል ኢኮኖሚ እና ለሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) መሠረታዊ ግብዓት በሆነበት በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኃይል ማዕከል የመሆን ሕልሟን ወደ እውንነት እየቀየረችው ነው።
ይህ እውነታ በወረቀት ላይ በሰፈሩ የይስሙላ ስምምነቶች ሳይሆን፣ በድንበር ተሻጋሪ የኤሌክትሪክ መስመሮች በተግባር የተመሰከረ ሐቅ ነው። ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት የተወሰዱት ቁርጠኛ እርምጃዎች ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ዋነኛ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ አስችለዋል።
የታላቁ የሕዳሴ ግድብ፣ የኮይሻ እና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሙላት ባለፈ፣ የቀጣናውን የጋራ ዕድገት የሚያረጋግጡ የትሥሥር ድልድዮች ሆነዋል። አሁን ደግሞ ይህ ቁርኝት ወደ ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጭምር መሻገሩ የነገውን ቀጣናዊ ትሥሥር ይበልጥ ብሩህ ያደርገዋል።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚደረገው ይህ ዘላቂ ትሥሥር፣ ከንግድ ልውውጥ እና ከገቢ ምንጭነት ባሻገር፣ አንዱ ሀገር ለሌላው የሕልውና ዋስትና የሚሆንበት እና የቀጣናውን ዘላቂ ሰላም በጽኑ መሠረት ላይ የሚገነባ ስልታዊ መሣሪያ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ረገድም ሀገራችን ከታሪካዊው የልመና አዙሪት ወጥታ በክብር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲን በቁርጠኝነት እየተገበረች ትገኛለች። የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን መተግበር፣ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት እና የብሪክስ አባል መሆን የኢትዮጵያን የፋይናንስ እና የኢንቨስትመንት አድማስ በሰፊው ከፍቶታል።
ይህ የፖሊሲ መዋቅር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ለመቶ ሺዎች ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም በጎረቤት ሀገራት ኢንቨስት በማድረግ አህጉራዊ የኢኮኖሚ አሻራቸውን እንዲያስፋፉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
የኢትዮጵያ የነገ ራዕይ ከአፍሪካ ቀንድ ተሻግሮ እስከ ሰሜን አፍሪካ እና አውሮፓ የሚዘልቅ ታላቅ የኃይል መረብ የመዘርጋት ታላቅ አልሚነት ነው። በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ከውኃ ኃይል በተጨማሪ በፀሐይ፣ በነፋስና በጂኦተርማል ኃይል ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት የታዳሽ ኃይል ብዝኃነትን በማረጋገጥ፣ ኢትዮጵያን የቀጣናው አስተማማኝ የኃይል "ባንክ" ያደርጋታል።
ይህ ዘላቂ ጉዞ ሀገራችንን ከተረጂነት አዙሪት ሙሉ በሙሉ በማውጣት፣ በዓለም አቀፍ መድረክ በራሷ የምትቆም፣ ክብሯ የተጠበቀ እና የምሥራቅ አፍሪካ የሰላም እና የብልጽግና ፋና እንድትሆን ያደርጋታል።
ምክንያቱም የዚህች ታላቅ ሀገር እውነተኛ እና ዘላቂ ብልጽግና ሊረጋገጥ የሚችለው፣ በራሷ አቅም በልጽጋ ለጎረቤቶቿም የብርሃን እና የዕድገት ዋስትና መሆን ስትችል ብቻ ነው ብለን እናምናለን።
የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል