የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ወቅት ሙያዊ ማብራሪያና ግንዛቤ ለሚሰጡ ምሁራንና የዘርፉ ልሂቃን ገለጻ ማድረግ ጀመረ።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ምሁራኑ በምክክር ሂደቱ ወቅት የሙያ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ተሳታፊዎች በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው የማድረግ ታላቅ ሚና ይኖራቸዋል።
ይህም ተሳታፊዎች ከስሜታዊነት በጸዳ፣ በዕውቀት ላይ በተመሠረተና በምክንያታዊነት ውሳኔዎችን እንዲያሳልፉ ለማስቻል የታለመ ነው።
ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሄደው በዚህ ዋና ጉባኤ ላይ ከ1 ሺህ 300 በላይ ወረዳዎች የተውጣጡ 4 ሺህ ተሳታፊዎች ይሳተፋሉ።
ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡት እነዚህ ተሳታፊዎች የተለያየ ሀገር በቀል ዕውቀት ያላቸው ቢሆንም፤ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር ምሁራኑ ውስብስብ የሆኑ ታሪካዊ አመጣጦችንና የታዩ ክስተቶችን በጥናት አስደግፈው በማብራራት ወደ መፍትሔ የሚያመላክት ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታትና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል ምቹ ምኅዳር መፈጠሩን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ለዚህም ላለፉት አራት ዓመታት ሰፊ የዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊዎች ልየታ ሥራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያን በሚመስልና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በተወከለበት መልኩ በ8 ቡድኖች በጥንቃቄ መደራጀቱ ተመላክቷል።
ተሳታፊዎቹ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ አዲስ አበባ መግባት እንደሚጀምሩና የምክክር ሂደቱ ቢያንስ ለ4 ሳምንታት እንደሚቆይ የገለጹት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ምሁራኑ በውይይት አጀንዳዎች ላይ መሠረታዊ ዕውቀት በማስጨበጥ የጋራ መረዳት እንዲፈጠር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
በመስከረም ቸርነት