Search

ከደን ጥበቃ እስከ ዘላቂ የውኃ ሀብት ልማት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ሳይንሳዊ እውነታዎች

ሓሙስ ሰኔ 25, 2018 71

የደን ሽፋንን ማሳደግ የውኃን መኖር፣ ጥራትና ተደራሽነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሻሽል በርካታ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጥናቶች ያመክታሉ።

በኢትዮጵያ በስፋት እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር እና የችግኝ ተከላ ሥራዎችም ከዘላቂ የውኃ ሀብት ልማትና ጥበቃ ጋር ቀጥተኛና ሳይንሳዊ ቁርኝት እንዳላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ከተለያዩ አካባቢያዊና ሃይድሮሎጂያዊ ጥናቶች በመነሳት፣ ችግኝ መትከል ለዘላቂ የውኃ ሀብት ጥበቃ ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚከተለው ማጠቃለል ይቻላል፡-

1. የከርሰ-ምድር ውኃን መሙላትና ማከማቸት

የሳይንስ እውነታዎች እንደሚያመለክቱት፤ የዛፎች ሥሮች የአፈርን መዋቅር በማላላትና ቀዳዳዎችን በመፍጠር የዝናብ ውኃ በቀላሉ ወደ መሬት ውስጥ እንዲሰርግ ያደርጋሉ። በዚህ ሂደት ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት ውኃው ከመሬት ወለል ላይ በጎርፍ መልክ ፈስሶ ከመባከን ይልቅ ወደ ከርሰ-ምድር በመግባት ተፈጥሯዊ የውኃ ማጠራቀሚያዎችን ይሞላል። ይህም ምንጮችና ጉድጓዶች በበጋ ወቅት እንኳ ሳይደርቁ ቀጣይነት ያለው ውኃ እንዲያመነጩ ያደርጋል።

2. ለአነስተኛ አርሶ አደሮች የውኃ አማራጭ መፍጠር

በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር፣ በዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ የነበረውን ባህላዊ የግብርና ሥራ በመቀየር ውኃን አቁሮ በዓመት ከሁለት እስከ ሦስት ጊዜ ለማምረት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል። በተለይም በአነስተኛ ማሳ ላይ ለሚከናወኑ የእርሻ ተግባራት አርሶ አደሮች የውኃ አማራጮችን እንዲያገኙ፣ በአቀበታማ መሬቶች ላይ ዛፍ መትከልና መንከባከብ ውኃን አስቀርቶ ለመጠቀም ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

3. የጎርፍ አደጋንና የገጽታ ፍሰትን መቀነስ

የዛፎች ቅጠሎችና ቅርንጫፎች የዝናብ ጠብታዎች በቀጥታ መሬት ላይ የሚያርፉበትን ኃይል ይቀንሳሉ። የደረቁ ቅጠሎችና ዕፅዋት ደግሞ በምድር ላይ የሚፈሰውን ውኃ ፍጥነት ይገቱታል። ይህም ከፍተኛ የጎርፍ አደጋን ከመከላከል ባለፈ፣ ውኃው ረጋ ብሎ ወደ መሬት እንዲሰረጽ ጊዜ ይሰጠዋል። ይህ ሂደት የወንዞችን መደበኛ የውኃ ፍሰት መጠን ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ እንዲሆን ያደርጋል።

4. የአፈር መሸርሸርን መከላከልና የግድቦችን ዕድሜ ማራዘም

የዛፎች ሥሮች አፈርን አጥብቀው የመያዝ ተፈጥሯዊ ባሕርይ አላቸው። ይህም በዝናብና በጎርፍ ምክንያት የሚመጣን የአፈር መሸርሸር በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። በዚህም ወደ ወንዞች፣ ሐይቆችና ሰው ሠራሽ የውኃ ግድቦች የሚገባውን የደለል መጠን ይገታል። ይህም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ሌሎች የሃይድሮ-ኤሌክትሪክና የመስኖ ግድቦች የውኃ የመያዝ አቅማቸው እንዳይቀንስና የዕድሜ ዘመናቸው እንዲረዝም ያደርጋል።

5. ተፈጥሯዊ የውኃ ማጣሪያ

የደን ሥነ-ምህዳር እንደ ተፈጥሯዊ የውኃ ማጣሪያ ያገለግላል። በጎርፍ አማካኝነት የሚመጡ የተለያዩ ኬሚካሎችን፣ አፈርና ቆሻሻዎችን የዛፍ ሥሮችና የአፈር ውስጥ ተሕዋሲያን በመምጠጥና በማጥለል ወደ ወንዞችና ሐይቆች የሚገባውን ውኃ ንጹሕ ያደርጉታል። ይህ አሠራር ለመጠጥ ውኃ የሚወጣውን የማጣሪያ ወጪ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል።

6. የአካባቢን እርጥበትና የዝናብ ዑደትን መጠበቅ

ዛፎች ከመሬት ውስጥ የሳቡትን ውኃ በቅጠሎቻቸው አማካኝነት ወደ አየር ያስወጣሉ፤ ይህ ሳይንሳዊ ሂደት ትራንስፒሬሽን  ይባላል። ይህ ሂደት በአየር ላይ ያለውን እርጥበት በመጨመር የደመና ምስረታንና የአካባቢን የዝናብ ዑደት ያፋጥናል። ደኖች የራሳቸውን ዝናብ የመሳብና የአየር ንብረትን የማቀዝቀዝ ከፍተኛ ተፈጥሯዊ አቅም አላቸው።

በአጠቃላይ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የደን ሽፋንን በማሳደግ ረገድ የሚጫወተው ሚና፣ የውኃ ሀብትን ከተፈጥሯዊ ምንጩ (ከዝናብና ከከርሰ-ምድር) ጀምሮ እስከ መጨረሻው መዳረሻ (ግድቦችና ወንዞች) ድረስ በዘላቂነት ለመጠበቅና ለማስተዳደር የሚደገፍ ቀዳሚ ሳይንሳዊ መፍትሔ መሆኑን ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

በመሐመድ ፊጣሞ