የኢትዮጵያ አዲሱ የልማት ጎዳና የተፈጥሮ ሀብትን ከዘመናዊ አኗኗር ጋር ያቀናጀ አዲስ ምዕራፍ ፈጥሯል።
ይህ ስትራቴጂያዊ አካሄድ የገጠር ኮሪደር ልማት እና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን በማስተሣሠር፣ የገጠሩን ማኅበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ እና የኢትዮጵያን ሥነ ምኅዳር በከፍተኛ ፍጥነት እየለወጠ ይገኛል።
ሁለቱ የኢትዮጵያ ትኩረቶች በተግባር ሲቀናጁ፣ የገጠር መንደሮችን ውበት ከመጨመር ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት እየጣሉ ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል፣ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማልማት እና የከርሰ ምድር ውኃን በማበልጸግ ረገድ ታላቅ ሀገራዊ አቅም ፈጥሯል።
ይህ ስኬት ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር በቀጥታ እንዲቆራኝ በመደረጉ፣ በኮሪደር ልማት የተገነቡት (እንደ ሀማሳ ሞዴል መንደር ያሉ) ዘመናዊ ስፍራዎች በአረንጓዴ ዐሻራ በለሙ አካባቢዎች ዙሪያ እንዲመሠረቱ መደረጉ ማኅበረሰቡ ንጹሕ አየር፣ ለም መሬት እና የተጠበቀ ተፈጥሮ እንዲኖረው አስችሏል::
ይህ የከተማን ውበት እና የተፈጥሮን ሕይወት ያጣመረ አዲስ የገጠር መንደር ገጽታ፣ ዜጎች ከቀድሞው አኗኗራቸው ወጥተው በክብርና በምቾት እንዲኖሩ ትልቅ ሥነ ልቦናዊ መነቃቃትን ፈጥሯል።
የዚህ የተቀናጀ ሥራ ትልቁ ስኬት የሚገለጠው በምግብ ዋስትና እና በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ ነው። በአረንጓዴ ዐሻራ የሚተከሉ ችግኞች አሁን ላይ ትኩረታቸውን ፍራፍሬዎች፣ የቡና ተክሎች እና ለንብ ቀፎዎች የሚሆኑ ዕፅዋት ላይ ማድረጋቸው፣ ለገጠር ኮሪደር ልማት ሞዴል መንደሮች ቀጥተኛ የሀብት ምንጭ ሆነዋል።
አርሶ አደሩ በኮሪደር ልማቱ ባገኘው ዘመናዊ መሠረተ ልማት ተጠቅሞ የአትክልት ስፍራዎችን፣ የተቀናጁ የንብ ቀፎዎችን እና የእንስሳት እርባታን ከአረንጓዴ ዐሻራ ውጤቶች ጋር በማጣመር በምግብ ራሱን እንዲችል አድርጎታል።
ይህ ሒደት ድህነትን ከመሠረቱ የሚነቅል፣ የዜጎችን ኑሮ በተግባር የሚቀይር እና የኢትዮጵያን የነገ ብልጽግና በጽኑ መሬት ላይ የሚያሳይ የለውጥ ማረጋገጫ ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: