ጎህ ሲቀድ በአሶሳ ከተማ አውራ ጎዳናዎች ላይ አንድ ለየት ያለ ትዕይንት ይታያል። አሽከርካሪዎችን በፈገግታ የሚቀበሉ፣ እግረኞችን በክብር የሚያሻግሩ እና "ቁም" እና "እለፍ" የሚሉ በእጅ የተሰሩ ምልክቶችን የያዙ ግለሰብ በሥራ ላይ ናቸው።
እኚህ ሰው አቶ አያሌው ደሳለኝ ይባላሉ። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፣ ከተማዋ በኮሪደር ልማት እያማረችና ጎዳናዎቿ እየሰፉ ቢመጡም፣ በዚያው ልክ እየጨመረ የመጣው የትራፊክ ፍሰትና የሚከሰቱ አደጋዎች እረፍት ነስቷቸዋል።
በክልሉ በ2018 ዓ.ም የ40 ሰዎች ህይወትን በአጭር የቀጠፈው የትራፊክ አደጋ፣ ከ44 ሚሊዮን 639 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የንብረት ውድመት አስከትሏል፡፡
ይህ ቁጥር ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ ኪሳራ መሆኑ የገባቸው አቶ አያሌው፣ አደጋው ከመከሰቱ በፊት መከላከል እንደሚቻል በማመን፣ የከተማዋ የትራፊክ መብራት እጥረትን በራሳቸው በጎ ፈቃደኝነት ለማስተማር ወስነዋል።
ያላቸውን ልምድና ክህሎት በመጠቀም የፈጠሯቸው ተንቀሳቃሽ የትራፊክ ምልክቶች ዛሬ የአሶሳ መጋቢ ጎዳናዎች መለያ ሆነዋል።
አቶ አያሌው "አንድም ሰው በግዴለሽነት ህይወቱ ማለፍ የለበትም" በሚል እምነት በየቀኑ በጎዳናዎች ላይ በመገኘት ለአሽከርካሪዎችና ለእግረኞች ተግባራዊ የግንዛቤ ትምህርት ይሰጣሉ።
የዚህ በጎ ፈቃደኛ ጥረት ምንጭ ደግሞ በክልሉ እየደረሰ ያለው አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ ነው። "ቴክኖሎጂውና ዘመናዊ የትራፊክ መብራቶች እስኪሟሉ ድረስ እጅና እግርን አጣጥፎ መቀመጥ አደጋውን ያባብሰዋል" የሚሉት አቶ አያሌው፣ እያንዳንዱ ዜጋ ለደኅንነቱ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በታላቅ ትጋት ይሰራሉ። የአቶ አያሌው ስጋት መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋርም የተቆራኘ ነው።
በክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አለማየሁ ኢማና እንደገለጹት፣ በክልሉ በ2018 ዓ.ም በደረሱ 66 የትራፊክ አደጋዎች ብቻ 31 ወንዶችና 9 ሴቶች በድምሩ የ40 ሰዎች ህይወት በአጭር ተቀጥፏል።
አደጋው በሰው ህይወት ላይ ብቻ ሳይወሰን በ57 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት፣ በ38 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት አድርሷል።
ከዚህም ባለፈ፣ በትራፊክ አደጋው ምክንያት ከ44 ሚሊዮን 639 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የንብረት ውድመት መድረሱ መመዝገቡንና ይህም ከክልሉ አልፎ ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ ኪሳራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአሶሳ ከተማ የሚታየው የኮሪደር ልማትና የጎዳናዎች ውበት፣ እንደ አቶ አያሌው ባሉ የከተማዋ "የመንገድ ላይ ጠባቂዎች" እና በታታሪ የትራፊክ ፖሊሶች ጥረት ታጅቦ፣ የሰው ህይወት የሚተርፍባት ከተማ እንድትሆን መሠረት እየጣለ ይገኛል።
አቶ አያሌው ደሳለኝ ለከተማው ነዋሪዎችና ለአሽከርካሪዎች የሚያስተላልፉት መልዕክት ዘወትር አንድ ነው፦ "ትራፊክ መከበር ያለበት ፖሊስ ሲኖር ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ህይወት ክቡር ስለሆነ ነው።"
የዚህ በጎ ፈቃደኛ ተግባር፣ የመንግሥት አካላት ዘመናዊ የትራፊክ መቆጣጠሪያ መሠረተ ልማቶችን እስኪያሟሉ ድረስ፣ በሰውኛ ርህራሄና በኃላፊነት ስሜት አደጋን እንዴት መቀነስ እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት እየሰጠ ይገኛል።
በጀማል አህመድ