ላሊበላ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ታላቅነት የሚያሳይ፣ የሰው ልጅ አስደናቂና ሕያው የሥራ ውጤት የሆነ ታላቅ ቅርስ መሆኑን ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የሀገራት አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት የዲፕሎማቲክ ልዑካን ቡድን አባላት ገለጹ።
ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የሀገራት አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች የዓለም ቅርስ የሆነውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የባህል ማዕከልን ጎብኝተዋል።
በዚህ የጉብኝት መርሃ ግብር ላይ 40 አምባሳደሮች እና ከ10 በላይ የሚሆኑ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የሀገራት አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት የዲፕሎማቲክ ልዑካን ቡድን አባላት በዚሁ ወቅት በሰጡት አስተያየት፤ ድንቅ የሆነውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጎብኘት በመታደላቸው የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ላይ የታደሙት የሜክሲኮ አምባሳደር አሌሃንድሮ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን እጅግ ረቂቅ የኪነ-ህንጻ ጥበብ አድንቀዋል።
ቅርሱ ከመሬት በታች ከአንድ ወጥ ዓለት ተፈልፍሎ የተሠራና "ወደ ሰማይ የሚናገር አስደናቂ የጥበብ ሚስጥር መገለጫ" ነው ብለዋል።
አምባሳደሩ አክለውም፣ እያንዳንዱ ማዕዘን፣ መስኮትና በር ከአንድ ነጠላ ድንጋይ የተቀረጸ በመሆኑ ለዓለም የሚታይ ታላቅ የአንድነት ምልክት መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር መሆኗንና እንደ ላሊበላ ያሉ ከምናብ በላይ የሆኑ አስደናቂ የጥበብ፣ የታሪክና የባህል ቅርስ ባለቤት መሆኗን በተግባር መመልከታቸውን አረጋግጠዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የሮማኒያ አምባሳደር ዩሊያና ግሊጋ በበኩላቸው፤ የቅርስ ጥበቃ ሥራ ታሪክን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአሁኑን እና የወደፊቱን ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ለመገንባት ያለፈውን ታሪክ ጠንቅቆ ማወቅ እንደሚያስፈልግ የገለጹት አምባሳደሯ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ቅርሶችን ለመጠገን እና ለመንከባከብ እያደረገ ያለውን ተገቢ ጥረት በማድነቅ፣ ይህን ዓይነቱን ለትውልድ የሚሻገር ታላቅ ሥራ ሁሉም አካል አጠናክሮ ሊያስቀጥለው እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተመሳሳይ በአፍሪካ ኅብረት የኩባ አምባሳደር ሉካስ ዶሚንጎ፣ ላሊበላ የአፍሪካን ታላቅነትና ቀደምት ስልጣኔ በግልጽ የሚያሳይ ሕያው ቅርስ መሆኑን አመልክተዋል።
አፍሪካ ለዓለም ሕዝብ ልታሳውቀው የሚገባ እጅግ የበለጸገ ባህል፣ ጥበብና ወግ ያላት መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ፤ አህጉሪቱን ሁልጊዜ ከችግርና ከቀውስ ጋር ብቻ አያይዞ የመግለጽ የተሳሳተ አመለካከት በአስቸኳይ መታረም እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
አፍሪካ በባህልና በታሪክ እጅግ ባለጸጋ መሆኗን ጠቅሰው፣ ይህንን እውነታ ለዓለም ለማስተዋወቅ ኢትዮጵያ የጀመረችው የቅርስ ጥበቃና የማስተዋወቅ ሥራ በሌሎችም በአርአያነት ሊወሰድ እንደሚገባ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።