ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ እና በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ የአፍሪካ ተምሳሌት እየሆነች መምጣቷን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የ"ፅዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ" 3ኛ ዙር ሀገር አቀፍ ንቅናቄን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።
ንቅናቄው ተራ የአንድ ፕሮግራም ማስጀመሪያ ብቻ አለመሆኑን ገልጸው፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ፣ የህዝብ ጤና እና የኢኮኖሚ ምርታማነት የሚወስን ታላቅ የጋራ ቃል ኪዳን ማደሻ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ባለፉት ሁለት ዙር ንቅናቄዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የተሳተፉባቸው ጠቃሚ ስኬቶች መመዝገባቸውን ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ሶስተኛው ዙር ንቅናቄ የቀደሙትን ጠንካራ ጎኖች በማጠናከርና እንደ ቀጣይነት ክፍተት እንዲሁም የተቋማዊ ቅንጅት ችግሮች ያሉ ውስንነቶችን በጥልቀት በመገምገም የተቀረፀ መሆኑን በዝርዝር አብራርተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት የተጀመረውና ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉበት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፣ ከተሞችን ውብና ለነዋሪዎች ምቹ ያደረጉት የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮግራሞች ለቱሪስት መስህብነትና ለደን ሽፋን ማደግ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።
ዛሬ የተጀመረው ንቅናቄም ከእነዚህ ሀገራዊ ተነሳሽነቶች ጋር በተቀናጀ መልኩ የሚተገበርና ጽዳትን ወደ ሀገራዊ ባህል ለመቀየር በከፍተኛ ደረጃ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
የንቅናቄው ቀጣይ ስኬት በሁሉም ክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች በሚወሰዱ ተጨባጭ እርምጃዎች ላይ የሚወሰን በመሆኑ፤ ክልሎችና ከተሞች ግልጽ የትግበራ ዕቅድና በጀት በመመደብ፣ ጠንካራ የክትትልና የሪፖርት ሥርዓት በመዘርጋት እንዲሁም የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች እና ከንቲባዎች የመሪነት ኃላፊነታቸውን በቅርበት እንዲወጡ አሳስበዋል።
ይህ ንቅናቄ የአንድ ተቋም ሳይሆን የመላው ሀገር ንቅናቄ በመሆኑ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪል ማህበረሰብ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና መላው ህዝብ በአንድነት እንዲንቀሳቀስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በአሸናፊ እንዳለ