Search

ከአየር ንብረት ጥበቃ እስከ ምግብ ዋስትና፤ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መዋቅራዊ ስኬቶች

ቅዳሜ ሰኔ 27, 2018 52

የተፈጥሮ መዛባትን መቋቋም፣ የአፈር መሸርሸርን መግታትና የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት መመከት የዚህ ትውልድ ትልቁ የህልውና ጥያቄ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ይህንን ዓለም አቀፋዊ ሥጋት ለመቀልበስና የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ ካቀረበቻቸው ታላላቅ ሀገራዊ መፍትሔዎች መካከል የ"አረንጓዴ ዐሻራ" መርሐ ግብር ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይዟል።

ይህ ታላቅ መርሐ ግብር ከተራ የችግኝ ተከላ ዘመቻነት ባለፈ፣ የሀገርን ገጽታ የቀየረ፣ የሕዝብን አንድነት ያጠናከረና በዓለም መድረክ አዳዲስ ሪኮርዶችን ያስመዘገበ ታሪካዊ የአረንጓዴ አብዮት መሠረት መሆኑ ተመላክቷል።

በሀገሪቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በ2011 ዓ.ም ሲጀመር በዚሁ የመጀመሪያ ዙር ላይ 23 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በመሳተፍ ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል።

በተለይም መርሃ ግብሩ በሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም “40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ” በሚል መሪ ሐሳብ ሲጀመር በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ታላቅ ታሪክ ተሠርቷል።

ይህም እ.ኤ.አ በሐምሌ 2017 በሕንድ ሀገር በተካሄደ የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ በ12 ሰዓታት ውስጥ 66 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወስን ኢትዮጵያ እንድትረከብ ያደረገ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከመጀመሪያው ምዕራፍ አንስቶ ከዓመት ዓመት የኅብረተሰቡን ተሳፎ እያሳደገ በስኬት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ በመጀመሪያዎቹ አራት ዓመታት ብቻ ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል የታቀደው ግብ ሙሉ በሙሉ ተሳክቷል።

በየዓመቱ በተለይም በክረምት ወራት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች እየተተከሉ የሚገኙ ሲሆን፣ በአንድ ቀን ሀገር አቀፍ መርሐ ግብሮች ላይ በአንድ ጀምበር በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ረገድ ኢትዮጵያ አዳዲስ የዓለም ታሪኮችንና ሪኮርዶችን ማስመዝገብ ችላለች።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ከሚተከሉ ችግኞች የመፅደቅ ዕድል ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩ ክፍተቶችን በመቅረፍ፣ ከተከላ በኋላ በሚደረግ ጥበቃና እንክብካቤ በአረንጓዴ ዐሻራ የተተከሉ ችግኞች የመፅደቅ መጠን በአማካይ ከ75 በመቶ እስከ 80 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል።

ይህ በጎ ተግባር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከመጀመሩ በፊት የነበረውን የሀገራችንን የደን ሽፋን በከፍተኛ ፍጥነት በማሳደግ አሁን ላይ ከ23.6 መቶ በላይ እንዲደርስ አስችሏል።

መርሃ ግብሩ መጀመሪያ ላይ ትኩረቱን በደን ልማትና አካባቢ ጥበቃ ላይ ብቻ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን ከፍተኛ መዋቅራዊ ለውጥ በማሳየት የአካባቢ ጥበቃን ከምግብ ዋስትና እና ከአርሶ አደሩ ገቢ ማሳደግ ጋር አያይዞታል።

ከተተከሉት ችግኞች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑና የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው እንደ ቡና፣ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ኮረሪማ እና ሌሎች የፍራፍሬና የቅመማ ቅመም ችግኞች ይገኙበታል።

በተጨማሪም በሺዎች የሚቆጠሩ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች በመቋቋማቸው ለሴቶችና ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን፣ የችግኝ ማፍላትና መሸጥ ሥራም አዲስና አዋጪ የገበያና የገቢ ምንጭ መሆን ችሏል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ የአፈር መሸርሸርን ለመቀነስና የከርሰ ምድር ውኃን ለማበልጸግ የጎላ አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል።

ይህ በላብና በጥረት የተመዘገበ ስኬት አገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በአረንጓዴ ልማትና በዲፕሎማሲ ረገድ ያላትን ተጽዕኖና ተሰሚነት ከፍ ያደረገው ሲሆን፣ አረንጓዴ ዐሻራ አሁን ላይ ተራ የተከላ ሥነ ሥርዓት መሆኑ ቀርቶ ነገን በዓይነ ሕሊና የገነባ አሻጋሪ ሀገራዊ እሴትና ለትውልድ የሚተላለፍ የማይጠፋ የሕይወት ቅርስ ሆኖ ቀጥሏል።

በሃይማኖት ከበደ