የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ በደህንነት እና ስትራቴጂ ጥናት ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 4ኛ ዙር የከፍተኛ መኮንኖች ስልጠና ተከታታዮችን ዛሬ ሰኔ 27 ቀን 2018 ዓ.ም አስመረቀ።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ተመራቂዎች በአመራርነት ሚናቸው የላቀ አስተዋፅኦ ለማበርከት በከፍተኛ ተነሳሽነት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ፊልድ ማርሻሉ በንግግራቸው፣ ለዘመናት በሰላም እጦት የሚገለጸው የቀይ ባሕርና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የደህንነት ሁኔታ ከምንጊዜውም በላይ እየተወሳሰበና የግጭት ቀጣና እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
አያይዘውም ታሪካዊ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያ አካባቢውን የማረጋጋትና የመሪነት ሚናዋን እንዳትጫወት፣ በውስጥ ጉዳዮች ብቻ እንድትጠመድ አበክረው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም ባሻገር ጎረቤቶቻችን እንዲታመሱ በማድረግ ለውስጣዊ ደህንነታችን ጫና ለመፍጠር የሚችሉ ሴራዎችን ወደ ግጭት እየቀየሩ ይገኛሉ ብለዋል።
ሀገራችንን ከባሕር ዳርቻ ለማስወጣት የተጠቀሙበት ዘለግ ያለ ዕድሜ የነበረው ጸረ-ኢትዮጵያ ቅንጅት፣ ዛሬ ደግሞ ስሙን ቀይሮ አዲስ የጥፋት "ጽምዶ" በመፍጠር ታሪካዊ የጸረ-ኢትዮጵያ ሴራውን በተግባር እያሳየ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
ያለ ጦርነት መዋል ማደር የማይችሉ፣ ሽንፈት የማያሳፍራቸውና ባንዳነትን የኑሮ ዘዴያቸው ያደረጉ አካላት የጠላት መጠቀሚያ ሆነው ሀገራቸውን እያዳከሙ መሆኑን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጠቁመዋል።
እነዚህ ኃይሎች የጠላትን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ወደ ጥፋት "ጽምዶ" በመግባት ሕዝባቸውን የሚያጎሳቁል እንዲሁም ልማትና ዕድገት እንዳይመጣ የሚያደርግ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን አብራርተዋል።
ይህ አካሄድ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ጥቅም ከማስገኘት ባለፈ፤ ለትግራይ፣ ለአማራና ለኦሮሞ ሕዝብ ከውድመት በስተቀር ምንም እንደማያመጣ በአጽንዖት ተናግረዋል።
የዘመኑ የጦርነት አካሄድ ካለፉት አራት የጦርነት ትውልዶች አካሄድ በእጅጉ የተለየ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ፣ ተመራቂዎች የወሰዱት ትምህርት የወታደራዊ ኃይል ቁልፍ የብሔራዊ ጥቅም ማስከበሪያ መሣሪያ መሆኑን አብራርተዋል።
ከኮሌጁ የቀሰሙት አጠቃላይ የደህንነትና ስትራቴጂክ ዕውቀት የአመራር አቅማቸውን በከፍተኛ ደረጃ ያሳደገ በመሆኑ፣ አሁን እየተሠራ ያለውን የሠራዊቱን የዝግጁነት ሥራ ይበልጥ እንደሚያጎለብተው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ተመራቂ መኮንኖች ወደ ስምሪት ሲወጡ ሠራዊቱ ወሳኝ የዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኝበት ወቅት መሆኑን በመገንዘብ፣ ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት በተግባር ከሚገጥሟቸው ሁኔታዎች ጋር ማዛመድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በውጤቱም ለውጡ በግልጽ የሚታይ የአመራር ሥራን በመሥራት የላቀ አስተዋፅኦ ለማበርከት በከፍተኛ ተነሳሽነት ሊተጉ እንደሚገባ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።