Search

የሀረሪ ክልል ካቢኔ የ2019 በጀት ከ12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሆን ወሰነ

ቅዳሜ ሰኔ 27, 2018 53

የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) የ2019 የክልሉ መንግሥት ረቂቅ በጀት ከ12 ቢሊዮን 8 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሆን ውሳኔ አሳተላልፏል፡፡

ካቢኔው በክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የቀረበለትን የ2019 የበጀት አመት ረቂቅ በጀት ላይ በጥልቀት በመወያነትና ግብዓት በማከል ለክልሉ ምክር ቤት መርቷል።

በዚህም መሰረት በክልል ደረጃ ከተያዘው በጀት 60 በመቶ ለካፒታል በጀት የተመደበ ሲሆን 38 በመቶው ደግሞ ለመደበኛ በጀት የሚውል ነው ተብሏል።

የበጀቱ ምንጭም በዋናነት በክልሉ ከተለያዩ ገቢዎች የሚሰበሰብ ገቢ እንዲሁም ከፌዴራል መንግሥት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር ለክልሎች የሚሰጥ ድጎማና ከሌሎች ምንጮች ታሳቢ መደረጉን ተገልጿል።

በጀቱ ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀርም የ33 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ነው የተገለፀው።

በዚህ ወቅትም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት በ2018 የበጀት አመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁና ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ስራ ትኩረት ይሰጣል። 

በተለይም በገጠርና በከተማ የሕዝብን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ሊመልሱ በሚችሉ ተግባራት ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ነው ያመላከቱት።

ለገጠር እና ለከተማ ኮሪደር ልማት፣ ለንፁህ መጠጥ ውሃ፣ ለትምህርትና ጤና ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

በጀቱ ቁጠባን መሰረት በማድረግ በተለይም የህዝቡን ህይወት በሚያሻሽሉና መሰረታዊ ጥያቄ በሚመልሱ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማስቻል አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።

በወረዳ ደረጃ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ ለማስጀመር ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ያመላከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህም ለህብረተሰቡ ፈጣን፣ ፍትሃዊና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

በክልሉ ገቢን አሟጦ ከመሰብሰብ አንፃር በትኩረት መንቀሳቀስ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም የክልሉ ኢኮኖሚ በሚያመነጨው ልክ በታቀደው ልክ መሰብሰብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱም በቀረበው የ2019 ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ክልሉ ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡