Search

መቐለ ዩኒቨርሲቲ ወደ ራስ ገዝነት እያመራ መሆኑን ባበሰረበት ዕለት 2,931 ተማሪዎችን አስመረቀ

ቅዳሜ ሰኔ 27, 2018 48

መቐለ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ባሳወቀበት ዕለት፣ በ33ኛ ዙር በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 931 ተማሪዎች አስመርቋል።

በዚህ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከተመረቁት መካከል 29 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል። ከተመራቂዎቹ ውስጥ 45 ተማሪዎች በሦስተኛ ዲግሪ (ፒኤችዲ)፣ 83 በስፔሻሊቲ፣ እንዲሁም 939 ተማሪዎች ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ናቸው።

 

በተጨማሪም ከተመራቂዎቹ መሀል 45ቱ ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ሲሆኑ ዩኒቨርሲቲው በታሪኩ እስካሁን ድረስ 150 ሺህ ተማሪዎችን በማስመረቅ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ሀገራዊ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፋና ሓጎስ (ዶ/ር) ተቋሙ ራስ ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የሚያስችለውን ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል።

ይህ ዕርምጃ ዩኒቨርሲቲው የፋይናንስ፣ የአካዳሚክ እና የአስተዳደር ነፃነት በማግኘት ራእዩን በላቀ ደረጃ እንዲያሳካ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርለት አብራርተዋል።

ከዚህም ባለፈ የትምህርት ጥራትን ይበልጥ ለማረጋገጥ እና የተመራቂዎችን የፈጠራ ክህሎት ለማሳደግ የሚያስችል ሰፊ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ መደረጉን ጠቁመው፣ ተመራቂዎቹ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ኅብረተሰቡን በቅንነትና በትጋት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።

በርካታ ፈተናዎችንና ውጣ ውረዶችን አልፈው ለዚህ ስኬት የበቁት ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው፣ የድካማቸውን ፍሬ በማየታቸው የተሰማቸው ደስታ ገልጸዋል።

በሙሉጌታ ተስፋይ