ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቱሪዝም ዘርፍ እያስመዘገበችው ያለው ስኬት እና እያከናወነችው ያለችው ሁለንተናዊ የሪፎርም ሥራ፣ በተጨባጭ ውጤቶች መታጀቡን ቀጥሏል።
ከእነዚህ አስደናቂ ስኬቶች መካከል በትናንትናው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ዘመናዊው የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት አንዱ ማሳያ ነው።
ፕሮጀክቱ በሀገራችን የተጀመረው የ‘ገበታ ለትውልድ’ መርሐ ግብር ያፈራው ሌላኛው ታላቅ ድል ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በቱሪዝም እና በመሠረተ ልማት ግንባታ ረገድ የጀመረችው ታላቅ ጉዞ በተገቢው ፍጥነት እና ጥራት እየሔደ መሆኑን በተግባር ያሳየ ሆኗል።
ይህ አዲስ ዘመናዊ ሪዞርት የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማስፋፋት ባለፈ፣ የሀገራችንን የኢኮኖሚ አቅም ከፍ የሚያደርጉ በርካታ ስትራቴጂያዊ ይዘቶችን አካትቶ ይዟል።
በአንድ ጊዜ ከ1 ሺህ 300 በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ የስብሰባ አዳራሽ የተገነባለት ሲሆን፣ በሐይቅ ላይ የተገነባው ልዩ ተንሳፋፊ ሬስቶራንት ደግሞ ለአካባቢው የተፈጥሮ ውበት ተጨማሪ ድምቀት ሆኗል።
ፕሮጀክቱ የአርባ ምንጭን የተፈጥሮ ፀጋ እና የቱሪስት መስህብነት ይበልጥ ከማስተዋወቁም በላይ፣ በአካባቢው ለሚገኙ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሰፊ እና ዘላቂ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የሚያበረከተው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እጅግ የጎላ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት መገንባት ኢትዮጵያ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያላትን ራዕይ በእጅጉ ያጠናክረዋል።
ከዚህ ቀደም ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እና ትልልቅ መድረኮች በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ተወስነው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ እንዲህ ያሉ ዘመናዊ ማዕከላት በክልል ከተሞች መገንባታቸው ከመዲናችን ባሻገር የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ትልቅ መሠረት ይጥላል። ይህም ኢትዮጵያን የአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ፣ እንዲሁም የታላላቅ መድረኮች እውነተኛ ማዕከል የማድረግ ራዕያችንን ይበልጥ እውን ያደርገዋል።
ይህ ፕሮጀክት ባለፉት ዓመታት በሀገራችን በተከናወኑ መጠነ ሰፊ የልማት ሥራዎች ውጤት የተገኘ አዲስ የሀገራችን ዕንቁ ስፍራ ነው።
መላው የሀገራችን ሕዝብ፣ የውጭ ሀገር ዜጎች እና የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ይህንን አዲስ መዳረሻ በመጎብኘት እና አገልግሎቶቹን በመጠቀም፣ ኢትዮጵያ የጀመረችውን አዲስ የቱሪዝም እና የኮንፈረንስ ምዕራፍ በጋራ እንዲቋደሱም ጥሪ ቀርቧል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ እና ባህላዊ እሴቶቿ ላይ በመመርኮዝ እያስመዘገበችው ያለው የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት፣ የሀገራችንን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ ወደፊት ለሚመጣው ትውልድ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም እና ኩራት ሆኖ የሚቀጥል ታላቅ ስኬት ነው።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: