በአሁኑ ወቅት በቀይ ባሕር እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የደኅንነት ስጋት እና ውስብስብ የጂኦፖለቲካዊ ፉክክር እየተባባሰ መጥቷል፡፡
ይህ ተለዋዋጭ የዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ እውነታ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን እና ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር የጸጥታ ተቋሞቻቸውን በየጊዜው ማሻሻል እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማዘመን እንዳለባቸው በግልጽ ያስገድዳል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ደግሞ ከአፍሪካ ቀንድ እና ከምሥራቅ አፍሪካ የጋራ ሰላም፣ ተጠቃሚነት እና ደኅንነት ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት ጠንካራ፣ ዘመናዊ እና አስተማማኝ ወታደራዊ አቅም መገንባት ለሀገራችን ኅልውና ወሳኝ እና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሆኗል።
ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የተተገበረው ሁለንተናዊ የጸጥታ ዘርፍ ሪፎርም፣ መከላከያ ሠራዊታችንን ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ነጻ አድርጎታል።
ዛሬ ላይ ሠራዊታችን በላቀ ቴክኖሎጂ፣ በሳይንሳዊ ምርምር እና በብቁ የሰው ኃይል የተገነባ የሕዝብ ተቋም ለመሆን ጠንካራ መሠረት ጥሏል።
የዚህ ሪፎርም ትልቁ እና መሠረታዊ ስኬት፣ ሠራዊቱ ከፓርቲ ታዛዥነት ወጥቶ ለሕገ መንግሥቱ እና ለሕዝብ ሉዓላዊነት ብቻ የሚቆም እውነተኛ ብሔራዊ ተቋም መሆን ማስቻሉ ነው።
ይህንን ስር ነቀል ለውጥ በሕግ ደረጃ ለማጽናት በወጣው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር 1286/2015 መሠረት፣ ሠራዊቱ ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ተጽዕኖ ነፃ ሆኖ ሀገራዊ ግዳጁን በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲፈጽም ጠንካራ የሕግ ከለላ ተሰጥቶታል።
መከላከያን በዘመኑ አቅም በማዘመን ረገድ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያሳየው እመርታዊ ለውጥ የሪፎርሙ ዋነኛ ማሳያ ነው።
አየር ኃይላችን አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ ወደ አምስተኛ ትውልድ (5th Generation) ዘመናዊ ተዋጊ አውሮፕላኖች ለመሸጋገር እና የተዋጊ አውሮፕላኖችን ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግ ስትራቴጂያዊ ፍኖተ-ካርታ ነድፎ እየሠራ ይገኛል።
አየር ኃይሉ ትናንት ከተጣለበት አዘቅት ወጥቶ አሁን የ4ኛ ትውልድ የአየር ቴክኖሎጂዎች ባለቤት ሆኗል፡፡
ዛሬ ላይ የታጠቃቸው እጅግ ዘመናዊ ተዋጊ እና ማሰልጠኛ አውሮፕላኖች፣ በሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) የተመዘገበው ግዙፍ አቅም እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ ውጊያ ሥርዓቶች አየር ኃይላችንን የቀጣናው ቀዳሚ እና ብቸኛ የሰማይ ላይ ጌታ አድርገውታል።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ እያደረገች ያለው ዝግጅት በየብስ እና በአየር ብቻ የተወሰነ አይደለም።
የሀገራችንን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ ፍላጎት እና የቀይ ባሕርን ጂኦፖለቲካዊ ትኩረት ከግምት በማስገባት፣ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በአዲስ መልክ በዘመናዊ አደረጃጀት እና በቴክኖሎጂ ተደግፎ ዳግም ተገንብቷል።
ይህ የባሕር ኃይላችን ዳግም መወለድ እና የሳይበር ደኅንነት አቅማችን በከፍተኛ ደረጃ ማደግ፣ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን እና የዲጂታል ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ ያላትን የማይናወጥ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
ሠራዊቱን ከዘመናዊ ተከላካይነት ባሻገር ግዙፍ የምርት ኃይል በማድረግ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተሄደበት ርቀትም እጅግ አስደናቂ ነው።
ስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን የያዙ፣ መረጃ የሚሰበስቡ፣ የሚከላከሉ እና የሚያጠቁ ድሮኖችን በሀገር ውስጥ ማምረት እና መገጣጠም መጀመሩ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ ትልቅ ምዕራፍ ነው።
የሆሚቾ አሙኒሽን ኢንጂነሪንግ ኮምፕሌክስ፣ ለሀገር ውስጥ ፍላጎት ጥይት ከማምረት ባለፈ 30 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ወታደራዊ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በመላክ ሀገራዊ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ማሳደግ ችሏል።
የጋፋት አርማመንት የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎችን በማምረት እንዲሁም የቢሾፍቱ ሞተራይዜሽን ተጥለው የነበሩ ከባድ መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ ጥገና መልሶ ለአገልግሎት በማብቃት የመከላከያችንን ራስን የመቻል አቅም በተጨባጭ አረጋግጠዋል።
ይህ ሁለንተናዊ ወታደራዊ አቅም በዕውቀት እና በጥናት የተደገፈ ዶክትሪን እንዲኖረው ሰፊ ሥራ ተሠርቷል።
የብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ እና የመከላከያ ዋር ኮሌጅ የደኅንነት እና ስትራቴጂካዊ ጥናቶችን በማካሄድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያላቸውን ብቁ አመራሮች በማፍራት ላይ ይገኛሉ።
ለረጅም ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የእጩ መኮንኖች ሥልጠና እንደገና ተጠናክሮ መቀጠሉ ወጣት መኮንኖችን በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እያንጸ ይገኛል።
ይህ ጠንካራ ዝግጅት ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የምታዋጣውን የሞተራይዝድ ሻለቃ በቢሾፍቱ በከፍተኛ ዝግጁነት አደራጅታ ቀጣናዊ ሰላምን ለማረጋገጥ ያላትን አቅም በተግባር እንድታሳይ አስችሏታል።
ባለፉት የሪፎርም ዓመታት የተመዘገቡት ድሎች የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን፣ ዘመኑን የዋጀ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና በከፍተኛ ወታደራዊ ሥነ-ምግባር የታነጸ መከላከያ ሠራዊት መገንባቱን በግልጽ ያረጋግጣሉ።
ይህ የፈጠራ፣ የዕውቀት እና የዝግጁነት አቅም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ የሚጠብቅ እና ሉዓላዊነቷ የማይደፈር ታሪካዊ ጋሻ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሀገራችንን በክፉ ሲያስቡ ሁለት ሦስት ጊዜ እንዲያስቡ እና እንዲጨነቁ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡
ይህ ደግሞ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ በግልጽ የተገለጠ ሲሆን፣ ግድቡ ኢትዮጵያ ማንኛውንም ልማቷን ለማደናቀፍ የሚሞክር ኃይል የማይበገር የብረት ክንድ እንደሚጠብቀው ያረጋገጠችበት ታላቅ ማሳያ ነው፡፡
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: