Search

የኢትዮጵያውያን የማይነጥፍ ጥበብ ከውቅር አብያተ ክርስቲያናት እስከ ተንሳፋፊው ሪዞርት

እሑድ ሰኔ 28, 2018 152

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ድንቅ የኪነ-ህንፃ ጥበብ ባለቤት በመሆን በዓለም ታሪክ ላይ ግዙፍ አሻራ ያሳረፈች ታላቅ ሀገር ናት።

በዩኔስኮ (UNESCO) ተመዝግበው የዓለምን ሕዝብ የሚያስደንቁት የአክሱም ሐውልቶች፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የፋሲለደስ ግንብ የዚህ ጥንታዊ ጥበብ ህያው ማሳያዎች ናቸው።

ከዚህም ባለፈ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣው የኮንሶ ማኅበረሰብ አስደናቂ የእርከን ሣራ እና የከተማ ግንባታ ጥበብ አባቶቻችን ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው ለመኖር የነበራቸውን የላቀ የምህንድስና ዕውቀት ያረጋግጥልናል።

የአሁኑም ትውልድ ከአባቶቹ የወረሰውን ይህንን የማይነጥፍ የምህንድስና ጥበብ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በማዋሃድ አዳዲስ ታሪኮችን እየጻፈ ይገኛል።

ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቆመን የገነባነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዘመናዊ የምህንድስና አቅማችንን ለዓለም ያሳየበት ትልቁ ማሳያችን ነው።

ይህ የፈጠራ እና የልማት መንፈስ ዛሬም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ቀጥሎ በቱሪዝም ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ እየከፈተ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በአርባ ምንጭ ያስመረቁት በሐይቅ ላይ የተገነባው ባለ 360 ዲግሪ ተንሳፋፊ እና ተሽከርካሪ ሬስቶራንት የዚህ አዲስ የፈጠራ ትውልድ ደማቅ መገለጫ ሆኖ ብቅ ብሏል።

ይህ አስገራሚ የመዝናኛ ማዕከል ተራ የህንፃ ግንባታ ሳይሆን የተፈጥሮን ውበት እና የሰውን ልጅ የምህንድስና ጥበብ በከፍተኛ ጥንቃቄ ያቀናጀ የዘመናችን የጥበብ ማሳያ ነው።

ማዕከሉ እጅግ ማራኪ የሆኑትን ታዋቂዎቹን 40 ምንጮች በጉልህ ለጎብኚዎች በሚያሳይ ስትራቴጂያዊ ስፍራ ላይ ማረፉ ለቦታው ልዩ ሳቢነትን አጎናጽፎታል።

በሐይቅ ላይ እየተንሳፈፉ እና እየተሽከረከሩ ተፈጥሮን ማድነቅ መቻል የቱሪዝም ልምድን ወደ አዲስ ከፍታ ያሸጋገረ ነው።

ይህ ሥራ በኢኮኖሚው ረገድ ለሀገር ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ግዙፍ አቅም ከመሆኑም ባሻገር፣ በኪነ-ህንፃ እና በግንባታው ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ነው።

ፕሮጀክቱ በተግባር ያረጋገጠው ትልቁ እውነት ኢትዮጵያውያን ድንቅ የዓለም አቀፍ ምህንድስና ጥበቦችን በሀገር በቀል አቅም መገንባት እንደሚችሉ ነው።

ማዕከሉ ከንግድ ሥራነቱ ባለፈ የኢትዮጵያውያን የመቻል እና የፅናት ተምሳሌት ሆኖ በታሪክ ውስጥ በጉልህ የሚቀመጥ ትልቅ ስኬት ነው፡፡

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: