ኢትዮጵያ ከሰኔ 26 እስከ 27 ቀን 2018 ዓ.ም. በጋና፣ አክራ "የወጣቶች ተሳትፎ ለአፍሪካ መረጋጋት" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው 3ኛው የአፍሪካ ኅብረት ሕገ-መንግሥታዊ ያልሆነ የመንግሥት ለውጥ የውይይት መድረክ ላይ ተሳትፋለች።
በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያን የወከሉት በአፍሪካ ኅብረት እና በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልእክተኛ አቶ በረከት ድሪባ ናቸው።
ምክትል ቋሚ መልእክተኛው ባደረጉት ንግግር፤ ሕገ-መንግሥታዊ ያልሆኑ የመንግሥት ለውጦችን ለመከላከል የወጡትን የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ማዕቀፎች በሁሉም ተቋማት ወጥነት ባለው መልኩ መተግበር እና ማስከበር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አቶ በረከት አክለውም በአንዳንድ የአፍሪካ አካባቢዎች በሕገ-መንግሥታዊነት እና በሕግ የበላይነት ላይ የተጋረጡ ስጋቶች እያደጉ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም ሕገ-መንግሥታዊ ባልሆነ የመንግሥት ለውጥ ሳቢያ ጉዳት ከደረሰባቸው ማኅበረሰቦች፣ በተለይም ከወጣቶች ጋር ያለውን ስትራቴጂያዊ ተግባቦት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ይህ መሆኑ ደግሞ ወጣቶች የኅብረቱን የሕግ ማዕቀፎች ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ሕገ-መንግሥታዊ ያልሆኑ የመንግሥት ለውጦችን በፍጹም ላለመቻቻል የተቀመጠውን አሕጉራዊ ፖሊሲ በጥብቅ መተግበር እንደሚገባ ያላቸውን ጽኑ ድጋፍ አረጋግጠዋል።
ይህ ሦስተኛው የአክራ የውይይት መድረክ፤ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት አባል ሀገራትን፣ የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች ተወካዮችን፣ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ወጣት አምባሳደሮችን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላትን እና ሌሎች የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በአንድ ላይ ያሳተፈ እንደነበር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: