የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማኅበራዊ ፍትሕን የማስፈን እና ለነዋሪዎች ክብር የመስጠት ሥራ አካል የሆነውን 30ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አስገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት አደረገ።
ማዕከሉን የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋ ሥራ አስጀምረዋል።
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ 4ኛ ቅርንጫፍ ሆኖ የተገነባው ይህ አዲሱ የምገባ ማዕከል ቀደም ሲል በቂርቆስ፣ በሸራተን ማስፋፊያ እና በካሳንቺስ አካባቢዎች የራሳቸው መኖሪያ ቤት ሳይኖራቸው በጥገኝነት እና በደባልነት ይኖሩ ለነበሩ አቅመ ደካሞች አገልግሎት የሚሰጥ ነው።
እነዚህ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም የከተማ አስተዳደሩ በአራብሳ አካባቢ ቤት ሠርቶ ያስገባቸው አረጋውያን እና ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ተጋልጠው የነበሩ ዜጎች መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዚህ ማዕከል ግንባታ ዓላማ "ከመመገብ ባሻገር" የሚል እሳቤ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።
ማዕከሉ የዜጎችን የዕለት ጉርስ ችግር በጊዜያዊነት ከማቃለል ባለፈ፣ ነዋሪዎቹ በዘላቂነት ቋሚ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር የተጀመረበት መሆኑንም አብራርተዋል።
በአዲስ አበባ እየተገነቡ የሚገኙት የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት የከተማ አስተዳደሩ ሰው ተኮር አሠራር በተግባር የሚገለጥባቸው መሆናቸውንም ከንቲባዋ አክለዋል።
በከተማዋ ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ባህል እያደገ መምጣቱን ያደነቁት ከንቲባ አዳነች፣ ያላቸውን በማካፈል ለተቋሙ ሥራ መጀመር አስተዋፅኦ ላደረጉ እንዲሁም በማዕከሉ በቋሚነት ዜጎችን ለመመገብ ቃል ለገቡ በጎ አድራጊ አካላት በሙሉ በተጠቃሚ ነዋሪዎች እና በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: