"ፖለቲካ ላይመች ይችላል፣ ግለሰብ ላይመች ይችላል፤ ሀገር ግን ሀገር ናት። የሀገርን ገጽታ፣ የሀገርን መልክ በሚያበላሽ መንገድ አንሂድ፤ እንሰልጥን፣ እንንቃ" የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት ነው፡፡
ይህ መልዕክት በፖለቲካ ሳይንስ እና በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ፍልስፍና ውስጥ መሠረታዊ እውነትን ያመላክታል።
መንግሥታት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መሪዎች ጊዜያዊ እና ተለዋዋጭ ሲሆኑ፣ ሀገረ-መንግሥት ግን የሕዝቦች የጋራ ታሪክ፣ ሉዓላዊነት፣ ባህል እና ዘላቂ ኅልውና መገለጫ ናት።
የጀርመናዊው ፈላስፋ ጆርጅ ዊሊያም ሄግል የሀገረ-መንግሥት ፍልስፍና እንደሚያሳየው ሀገር የማኅበረሰቡ ከፍተኛው የጋራ ኅልውና መድረክ ነች።
በመሆኑም በወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ላይ የሚኖረንን ቅሬታ የሀገርን መልክ ወደ ማበላሸት ደረጃ ማሸጋገር የሲቪክ ንቃት ጉድለትን ያሳያል።
የውስጥ ቅሬታዎችን ተገን አድርጎ የሀገርን ስም ማጠልሸት፣ የጋራ ቤትን በእሳት እንደማያያዝ ይቆጠራል።
የልማት ጉዞ እና የሀገር ገጽታ
ይህንን ፍልስፍና ከኢትዮጵያ ተጨባጭ የልማት ጉዞ ጋር ስናስተሳስረው፣ የሀገርን ገጽታ በአዎንታዊ መልኩ ለመለወጥ የሚከናወኑት ሥራዎች ከፖለቲካ ፓርቲዎች ወገንተኝነት የላቁ መሆናቸውን እንረዳለን።
በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ አዲስ አበባን ለአፍሪካ ከተሞች የለውጥ ፋና ወጊ እያደረጋት ነው።
የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ አዲስ አበባ የፓን አፍሪካኒዝም ጽኑ መሠረትነቷን በልማቷ ዳግመኛ አስመስክራለች ሲሉ የገለጹበት መልዕክት ይህንኑ እውነታ ያረጋግጣል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ አመንጪነት የተገነቡት የገበታ ፕሮጀክቶች የሀገራችንን የቱሪዝም ካርታ ከመሠረቱ የቀየሩ የጋራ በረከቶቻችን ናቸው።
በዚህም ምክንያት፣ እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት ከ1.4 ሚሊየን በላይ የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡
ከዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ቱሪዝም እና ከውጭ ጎብኚዎች ከ5.2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱም የዚህ የገጽታ ግንባታ ሥራ ፍሬ ነው።
ዲጂታል ዲፕሎማሲ እና ሀገራዊ መግባባት
በ21ኛው ክፍለ ዘመን የለስላሳ ኃይል (Soft Power) እና የዲጂታል ዲፕሎማሲ የሀገራትን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።
እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ ያሉ ሀገራት የጉዞ ቪሎገሮችን ተጠቅመው ስለ ልማታቸው አዲስ ትርክት እየገነቡ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያም የዓለም ታዋቂ ሰዎችን ተፅዕኖ በመጠቀም የቆየውን የድህነት ትርክት በአዎንታዊ የልማት ገጽታ ለመተካት እየሰራች ትገኛለች።
ይህንን ጥረት በፖለቲካዊ ጥላቻ ለማጣጣል መሞከር የዘመናዊነትን ጉዞ ካለመረዳት ይመነጫል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በነዳጅ አቅርቦት ላይ ያላት ጥገኝነት እና የጎረቤት ሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ያስከተለው ጫና የመሳሰሉ ከባድ ጂኦ-ፖለቲካዊ ተጋላጭነቶች አሉባት።
እነዚህን ሁሉ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ፈተናዎች ለማለፍ መንግሥት ውጤታማ ጥረት እያደረገ ፈተናውንም እያለፈ ይገኛል።
ማንኛውም ዜጋ ቢሆን እንዲህ ባሉ ፈታኝ ወቅቶች ሀገርን ለውጭ ጫና ተጋላጭ ማድረግ ሳይሆን፣ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በአንድነት መቆም የኅልውና ጉዳይ ነው።
"ሀገር ግን ሀገር ናት" የሚለው መሠረታዊ ጥሪ ሁላችንም ከፖለቲካዊ ልዩነቶች በላይ ለሆነው ብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ እንድንሰጥ የሚያስገድድ ነው።
በአሁኑ ወቅት የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ጊዜያዊ የፖለቲካ ውጥረቶች ወደ ሀገራዊ ውድመት እንዳያመሩ እና የተፈጸሙ ስህተቶች ታክመው ቁስሎች እንዲሽሩ የሚያስችል ታሪካዊ መድረክ ነው።
እነዚህን ኢትዮጵያ በሺህ ዘመናት አንዴ ያገኘቻቸውን ዕድሎች በመጠቀም ሀገራችንን ወደ ልዕልናዋ መመለስ ምንም ድርድር የማይደረግበት ጉዳይ ነው፡፡
የፖለቲካ ሥርዓቶች እና መሪዎች ያልፋሉ፤ ሀገር ግን በልጆቿ የጋራ ጥረትና ገጽታ ግንባታ ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: