Search

በጠረጴዛ ዙሪያ የሚገነባው የኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት

እሑድ ሰኔ 28, 2018 111

ኢትዮጵያ በታሪኳ ያጋጠሟትን ውስብስብ እና መዋቅራዊ የፖለቲካ ልዩነቶች በዘላቂነት በመፍታት አስተማማኝ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የጀመረችው ሀገራዊ ውይይት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ብቸኛው እና አማራጭ የሌለው ስልታዊ መንገድ ነው።

ይህ ታሪካዊ መድረክ በኃይል እና በግጭት የሚመራውን የቆየ እና አጥፊ የፖለቲካ ባህል በመለወጥ ዜጎች እና የፖለቲካ አቀንቃኞች በሐሳብ ልዕልና እንዲሁም በሰለጠነ መንገድ እንዲወያዩ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

ምክክሩ ለዘመናት የዘለቁ የፖለቲካ ቁስሎችን በማዳን የኢትዮጵያን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስን ጽኑ መሠረት ይጥላል።

ታሪክ እንደሚመሰክረው ኢትዮጵያውያን ለውይይት እና ለዕርቅ አዳዲስ አይደለንም። የገዳ ሥርዓት፣ በየአካባቢው ያለው የሽምግልና ባህላችን፣ የጉራጌው የጆካ እና ሌሎችም ሀገር በቀል እሴቶቻችን ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት የላቀ ጥበባችንን ያሳያሉ።

የዛሬው ሀገራዊ ምክክርም እነዚህን የነጠሩ ባህሎቻችንን ከዘመናዊ የዴሞክራሲ መርሆች ጋር በማዋሃድ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እንዲሰፍን የሚያደርግ ዋነኛ መሣሪያ ነው።

ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በማዳመጥና በጋራ ስምምነት መፍታት መቻል የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዋነኛ መገለጫ ነው።

ሀገራዊ ምክክሩም የፖለቲካ ኃይሎች ከጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት ወጥተው ለሀገር የጋራ ደኅንነት እና ለሕዝብ ሁለንተናዊ ጥቅም ቅድሚያ እንዲሰጡ የሚያስገድድ አዲስ የፖለቲካ ሥነ-ምኅዳር እያጎለበተ ይገኛል።

በተለያዩ ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ትርክቶች መካከል ቁርሾዎች መፍትሔ ካልተሰጣቸው የማይናወጥ ጠንካራ ሀገር መገንባት እንደማይቻል የዓለም ታሪክ በግልጽ ያሳየናል።

በመሆኑም አሁን የሚደረገው ምክክር በዋና ዋና ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባቢያ ነጥቦችን በማስቀመጥ የሀገርን ሉዓላዊነት እና አንድነት በማይናወጥ መሠረት ላይ የሚተክል ሂደት ነው።

ይህ የሰላም ጉዞ በጋራ እሴቶች ላይ የተገነባች፣ ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት የምታሳትፍ እና ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ የሚደረግ ታሪካዊና ወሳኝ እርምጃ ነው፡፡

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: