ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ፣ የዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ በርካታ ትምህርቶች የተገነዘቡበት እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የኖረውን ድልብ የሀገር ግንባታ ባሕል በተግባር ያረጋገጠበት ታሪካዊ ሁነት መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ወቅት፣ ምርጫው ራሱ የጥቃት ዒላማ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን የተሰነዘረውን ጥቃት በጽናት መክቶ አሸናፊ መሆን መቻሉን አስታውቀዋል።
"በዘንድሮው ምርጫ አይሳካም" የሚለው አፍራሽ ሐሳብ የብዙዎች ድምፅ ሆኖ በነበረበት ወቅት፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም ጽንፈኝነትን በተግባር ውድቅ ማድረጋቸውንም አብራርተዋል። ለዚህም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
በምርጫው ሂደት ላይ የታየውን ሕዝባዊ ተሳትፎ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ አዛውንቶች፣ ታማሚዎች፣ ሐዘንተኞች እና እመጫቶች ጭምር በከፍተኛ ስሜት እና ቁርጠኝነት መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።
ይህ የታየው ከፍተኛ ድምፅ እጅግ ታላቅ መልዕክት ያዘለ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት ይህንን የሕዝብ ውሳኔና ድምፅ በግዴለሽነት እንደማይመለከተውና ከፍተኛ ክብርና ዋጋ እንደሚሰጠው በቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
"ይህንን የሕዝብ ታላቅ ድምፅ አቅልለን አንወስደውም፤ ትልቅ ክብር እንሰጣለን።" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጠናቀቀው ምክር ቤት ውስጥ ለነበራቸው ቆይታ የምክር ቤቱ አባላት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ላቅ ያለ ምሥጋና አቅርበዋል።
አያይዘውም በቀጣዩ የሥራ ዘመን በምክር ቤቱ ውስጥ የማይቀጥሉትን አባላት ጨምሮ፣ ሁሉም ወገኖች ወደፊትም ለሀገር ግንባታና ለሕዝብ አገልግሎት የሚያደርጉትን ንቁ ተሳትፎና በጎ አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: