Search

ሃይማኖቶች የሰላም እሴቶች እንጂ የግጭት ምንጮች አይደሉም፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ማክሰኞ ሰኔ 30, 2018 142

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 30 መደበኛ ስብሰባ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ሃይማኖትን እና ሀገራዊ ሰላምን አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያ በሃይማኖታዊ እሴቶች የታነጸች ሀገር መሆኗን ገልጸው፣ ሀገር በመሰረተ ልማት ብቻ እንደማትገነባ አስገንዝበዋል።

ይልቁንም ባህልና እሴቶችን የሚገነቡ ተቋማት ለሀገር እንደሚያስፈልጉ በመጠቆም፣ ሃይማኖታዊ ተቋማት ለሀገር ግንባታ ያላቸውን ዘርፈ-ብዙ ፋይዳ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ታሪክ ውስጥ የሰላም እና የትብብር ዘመናት የበዙ ቢሆኑም አልፎ አልፎ የግጭት ታሪኮች እንደነበሩ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሆኖም ሃይማኖቶች ከተፈጠሩት የግጭት ሁኔታዎች ተምረው፣ ታርቀውና ተቻችለው አብረው የኖሩባቸው ጊዜያት እጅግ ረጅም መሆናቸውን አስታውሰዋል።

አክለውም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋሉ አብዛኛዎቹ ግጭቶች በአራት ዋና ዋና መንስኤዎች የሚነሱ ቢሆንም፣ ብዙውን ጊዜ ግን የጥፋት ኃይሎች ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲሉ ግጭቶችን በሃይማኖት እና በብሔር ሽፋን እንደሚደብቁት አስረድተዋል።

በሀገራችን እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶችን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "ነውጠኞች በየአካባቢው ክብሪት ይዘው ግጭት እየለኮሱ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጀሌዎቻቸው አዲስ አበባ ተቀምጠው በማኅበራዊ ሚዲያና በተለያዩ መንገዶች ግጭቱን እያባባሱ ይገኛሉ" ብለዋል።

በተለይም በምርጫ ወቅት በአንዳንድ የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የጦር መሳሪያዎች ተደብቀው እንደነበር በማንሳት ድርጊቱን ኮንነዋል።

ከሃይማኖት ግጭት የሚገኝ አንዳችም የፖለቲካ ትርፍ እንደሌለ ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በሁከትና በብጥብጥ የሚሞተው ወንድማማች ሕዝብ በመሆኑ ሁሉም ወገኖች ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት በሃይማኖት ግጭት በቀጥታ የተሳተፉ 22 ተጠርጣሪዎች እና ሁኔታውን ከአዲስ አበባ ሆነው ያባባሱ አካላት በሕግ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙም ይፋ አድርገዋል።

ግጭት ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ከነበሩ ዜጎች መካከል 90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወደ ቀያቸው መመለሳቸውንና ቀሪዎቹንም ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ ላይ ተቀምጠው የሃይማኖት ግጭት ለሚያስነሱና ለሚያባብሱ አካላት በሙሉ ከጥፋት ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ አሳስበዋል።

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: