Search

የሀገር መከላከያና የጸጥታ አካላትን ማክበር የሥልጣኔ ምልክት ነው፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር )

ማክሰኞ ሰኔ 30, 2018 162

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የኢትዮጵያን መከላከያና የጸጥታ አካላትን ማክበር የሥልጣኔ ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።

በሰለጠነው ዓለም ዜጎች የመከላከያ ሠራዊትን ጀግንነትና የሚከፍሉትን ዋጋ እያወደሱ፣ መንግሥትን ወይም ፖሊሲ አውጪዎችን መቃወም በሚገባቸው መድረክ ደግሞ ይቃወማሉ ይህም ትልቅ የሥልጣኔ ምልክት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በአንጻሩ በኢትዮጵያ ለሀገር ዘብ የቆመውንና የሞተልንን የመከላከያ ሠራዊት እንደ ገዳይ መቁጠር ያለመሰልጠንን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሕይወታቸውን ጭምር መሥዋዕት በማድረግ ኢትዮጵያን የሚያቆሙ ሰዎችን አለማክበር እንዲሁም ተቋማትን ለማፍረስ መሞከር በአስቸኳይ ሊታረም የሚገባው ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በምርጫ ወቅት ተጠንስሰው ስለነበሩ የጸጥታ ስጋቶች በሰጡት ማብራሪያ፣ በአርሲ ዞን ምርጫውን ለማደናቀፍ ከፍተኛ የጥፋት ዝግጅት ተደርጎ እንደነበር ይፋ አድርገዋል።

በዚህም ሴራ ውስጥ በአንዳንድ የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር በርካታ ቦንቦች እና ጠመንጃዎች ተደብቀው መገኘታቸውን ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ ከአርሲ በተጨማሪም በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር እና በጎንደር ከተሞች በተመሳሳይ መልኩ ረብሻ ለመፍጠር የታቀዱ ሰፊ እቅዶችና በምርጫ ጣቢያዎች ላይም የተጠነሰሱ ሴራዎች እንደነበሩ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በመንግሥትና በጸጥታ አካላት በተደረገው ከፍተኛ ጥንቃቄና ዝግጅት የተጠነሰሱትን የጥፋት ሴራዎች በሙሉ ማክሸፍ መቻሉን አስታውቀዋል።

በአርሲ ዞን ውስጥ ሕዝቡን አደጋ ላይ ለመጣል ወደ መንደር የገቡ የጥፋት ኃይሎች ሕዝብን ለመከላከል በቁርጠኝነት ከቆመው የጸጥታ ኃይል ጋር ባደረጉት ግጭት በጥቅሉ 11 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ሕይወታቸው ካለፈው ዜጎች መካከል ስምንቱ የኢትዮጵያ መከላከያን ደግፈው የተሰለፉ የሚሊሻና የፖሊስ አባላት መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህ የጸጥታ አካላት ራሳቸውን መሥዋዕት በማድረግ የብዙ ንጹሐን ዜጎችን ሕይወት የታደጉ ታላቅ ባለውለታዎች በመሆናቸው መላው ሕዝብ ከፍተኛ ክብርና አድናቆት ሊቸራቸው እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: