ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት የተከተለው ብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሪፎርም በአሁኑ ወቅት ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጣ መሆኑን አስታውቀዋል።
አጠቃላይ የዓለም ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች በሀገራችን ላይ ተጽዕኖ ማሳረፋቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሆኖም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከናወኑት መጠነ ሰፊ የሪፎርም ሥራዎች ምክንያት ኢትዮጵያ በፅናት እንድትቀጥልና ለውጥ እንድታስመዘግብ አስችሏታል ብለዋል።
በመሆኑም የተወሰዱት ጠንካራ የሪፎርም እርምጃዎች ከመንግሥት ሚና ባለፈ የሀገርን መጻኢ ዕድል መለወጥ ላይ ያለመ እና ተስፋን የሰነቀ መሆኑን አብራርተዋል።
በተለይም በግብርናው ዘርፍ የተከናወኑ ዘመናዊ የኩታ ገጠም እርሻዎች፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የመስኖ ልማት፣ የእርሻ መሬት ማስፋፋት እና የምርጥ ዘር አቅርቦት ሥራዎች ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዝርዝር አስረድተዋል።
በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ዘንድሮ 29 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ ወደ 1.3 ቢሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ለመሰብሰብ መቻሏን ይፋ አድርገዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው ተቋርጦ እና ቆመው የነበሩ በርካታ ግድቦች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው ለአጠቃላይ የግብርናው ዘርፍ መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል።
እነዚህን ተጨባጭ ለውጦች ተከትሎም በዘንድሮው ዓመት የግብርናው ዘርፍ 7.7 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅ እነዚህ አመላካቾች ማሳየታቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር እና የፍራፍሬ ልማት አስደናቂ እምርታ እያሳየ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አመልክተዋል።
ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአቮካዶ ምርት ከአፍሪካ ሁለተኛዋ ከፍተኛ ላኪ መሆን መቻሏ እና ከዘርፉም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እያገኘች መሆኑ ነው።
ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በድርቅ እና በአስቸጋሪ የአየር ንብረት ሁኔታ ይታወቅ የነበረው የቦረና ዞን በአሁኑ ወቅት ሰፊ የስንዴ ማሳ የተገኘበት መሆኑን እንዲሁም በሶማሊ ክልልም በተመሳሳይ ሰፋፊ የስንዴ እርሻዎች እየለሙ መሆናቸውን በማሳያነት አንስተዋል።
ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ሁኔታ እየዋዠቀ ባለበት በዚህ ፈታኝ ወቅት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሀብት እየተንቀሳቀሰ እና በርካታ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች እየተገኙ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አረጋገጠዋል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: