Search

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከለውጡ በፊት ከነበረው አቅምና ማጓጓዝ በትንሹ በሦስት እጥፍ አድጓል፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ማክሰኞ ሰኔ 30, 2018 130

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከለውጡ በፊት ከነበረው አቅምና አሠራር አንጻር ሲታይ የማጓጓዝ አቅሙ በአሁኑ ወቅት በትንሹ በሦስት እጥፍ ማደጉን አስታውቀዋል።

አየር መንገዱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 17 ሚሊዮን ገደማ የውጭ ሀገር መንገደኞችን እና 4 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ተጓዦችን በድምሩ ወደ 21 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ማጓጓዝ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ይህ የስኬት ጉዞ አየር መንገዱ ቀደም ሲል ከነበረበት አፈጻጸም የሦስት እጥፍ ዕድገት ያሳየበትና በዚያው ልክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬና ሀብት ያስገኘ መሆኑን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ 200 በላይ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች መካሄዳቸውን ጠቅሰው፣ በእነዚህ መድረኮች ላይም በርካታ መቶ ሺህ የውጭ እንግዶችና ተሳታፊዎች በከፍተኛ መስተንግዶ ማለፋቸውን ጠቁመዋል።

ይህ የቱሪዝምና የስብሰባዎች መነቃቃት ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ትልቅ መሠረት መሆኑን በማብራራት፣ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት የአገልግሎት ዘርፉ 9 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

አጠቃላይ የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ እንዲሁም የፍላጎትና አቅርቦት የመጨረሻ ማጠቃለያ መረጃ በመስከረም ወር የሚወጣ ቢሆንም፣ አሁን ያሉት አበረታች አመልካቾች ግን የኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት 10 ነጥብ 3 በመቶ ገደማ ሊደርስ እንደሚችል ያሳያሉ ብለዋል።

ይህም አፈጻጸም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ደረጃ ትልቁን የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበች ሀገር የሚያደርጋት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ይህም መንግሥት ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማምጣት የገባውን  ቃል በተግባር ያሳካበት ታላቅ ማረጋገጫ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው አብራርተዋል።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: