የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በርካታ ውጤቶችን ያስገኘ እና መንግሥት ለሰላም ያለውን ጽኑ ፍላጎት በተግባር ያሳየበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ሕወሓት የትግራይ ወጣቶችን በግዳጅ እየመለመለ ለሱዳን በመሸጥ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ብዙዎች ተጠቃሚ የሆኑበትና ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶች ዳግም እንዲጀመሩ ያስቻለ ትልቅ የሰላም ትሩፋት እንደሆነም አብራርተዋል።
መንግሥት ለሰላም ዘላቂነት ሲል ጦርነት ሊያስነሱ የሚችሉ በርካታ ትንኮሳዎችን በከፍተኛ ትዕግስት ማለፉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በጦርነቱ ወቅት የተማረኩ ታጣቂዎችን በሰላም ወደ ማኅበረሰቡ ቢቀላቅልም፣ የተለቀቁት ኃይሎች ዳግም ወደ ስፍራው ተመልሰው ችግር እየፈጠሩ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም መንግሥት ለሰላም እና ለቤተሰቦቻቸው ሲባል የወንጀለኞቹን ንብረት ጭምር ሳያግድባቸው መቆየቱን ጠቁመው፣ ነገር ግን ወንጀለኞቹ አሁንም ፀረ-ሰላም እንቅስቃሴያቸውን በመቀጠላቸው የችግሩ ፈጣሪ ያልሆነው የትግራይ ሕዝብ ክፉኛ እየተጎዳ ይገኛል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የሕወሓት ቡድን ወደ ባሰ ወንጀል መሸጋገሩን በማብራሪያቸው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ቡድኑ የትግራይ ወጣቶችን በግዳጅ እየመለመለ ለሱዳን በመሸጥ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ በመላው የትግራይ አካባቢዎች አፈሳ በስፋት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም የተነሳ የትግራይ ልጆች አሁን ላይ በሰላም እየኖሩ ያሉት ከክልላቸው ውጭ በሆኑ የሀገራችን አካባቢዎች ብቻ መሆኑን አብራርተዋል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: