Search

ሕገ መንግሥቱን ቀድዶ መጣል ሳይሆን መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች ካሉ በሕዝብ ውሳኔ ማሻሻል የመንግሥት አቋም ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ማክሰኞ ሰኔ 30, 2018 106

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው በተለይም እየተካሄደ ስላለው ሀገራዊ ምክክር እና ስለ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ የመንግሥታቸውን ቁልፍ አቋሞች በዝርዝር አብራርተዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ ዙሪያ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ ታሪካዊ መድረክ ኢትዮጵያን ወደፊት ሊወስዳት የሚችል እና በቀጣይ ለሀገራችን የሚበጀውን አዎንታዊ አቅጣጫ የሚያሳይ ጠንካራ ምክረ ሀሳብ ይዞ እንደሚወጣ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የሚታዩት ችግሮች በሙሉ አሁን ባለው መንግሥት የተፈጠሩ ባይሆኑም፣ እነዚህን ለዘመናት የተከማቹ ውስብስብ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት በትኩረት እና በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

መንግሥት መሰል ሀገራዊ ውይይቶችን እና ምክክሮችን በሙሉ ልብ የሚደግፈውም እነዚህን የተከማቹ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እና በጋራ መፍትሔ ለመቅረፍ ካለው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህንኑ ሀሳብ ሲያጠናክሩም፣ "ይህንን ሰፊ ሀገራዊ ዕድል በመጠቀም፣ ካለፉት እሰጥ አገባዎች ወጥተን በሰለጠነ መንገድ መወያየት ይኖርብናል፤ ዋናው መገንዘብ ያለብን ነጥብ አሁን የምንመክረው የአንድን ጊዜያዊ ገዥ ፓርቲ ስህተት ለማረም ብቻ ሳይሆን፣ ለዘመናት የተከማቹ ስር የሰደዱ ሀገራዊ ችግሮቻችንን በጋራ ጠረጴዛ ዙሪያ ፈትተን፣ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሚበጅ አዲስ ማህበራዊ ውል ለመፈረም ነው" ብለዋል።

ይህ ሀገራዊ ምክክርም በመወያየት፣ በመነጋገር እና በመተማመን እንዴት አብሮ መኖር ይቻላል ለሚለው ታሪካዊ ጥያቄ ዘላቂ ምላሽ የሚሰጥበት ብቸኛው መንገድ መሆኑን አብራርተዋል።

የሕገ መንግሥት ማሻሻያን በተመለከተ የመንግሥታቸውን ግልጽ አቋም ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያሉትን አዎንታዊ እሴቶች ይዘን እንቀጥላለን፤ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን ነጥቦች ደግሞ ማንንም በማይጎዳ፣ የሁሉንም መብት በሚያከብር እና አንድነታችንን በሚያጠናክር መልኩ እናሻሽላለን" ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት ሰነዱን ሙሉ በሙሉ ቀድዶ መጣል ሳይሆን፣ የተሻሉትን እና ሀገርን የሚጠቅሙትን ድንጋጌዎች አስቀጥሎ መጓዝ የመንግሥታቸው አቋም መሆኑን ጠቅሰዋል።

መሻሻል እና መታረም ያለባቸው አንቀጾች ካሉ፣ ያለምንም መሸራረፍ በሕዝብ ቀጥተኛ ውሳኔ እና ፍላጎት ላይ ተመስርተው ማሻሻል እንደሚገባ በማብራሪያቸው አስረድተዋል።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: