ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከብራዚል እና ኮሎምቢያ በመቀጠል በዓለም 3ኛዋ ትልቋ የቡና ላኪ ሀገር ደረጃ ላይ መቀመጧን እና በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚዋ (1ኛ) መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ገለጹ።
ሀገራችን በዚህ ዓመት ብቻ ከቡና የወጪ ንግድ 3.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ ገቢ ሀገራችን ከዚህ ቀደም ባለፉት 17 ተከታታይ ዓመታት በድምሩ ከቡና ኤክስፖርት ካገኘችው 3.3 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር በዘርፉ የተመዘገበውን ግዙፍ ዕድገት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የኮፊ ዓረቢካ መገኛ እና በየትኛውም ዘመን ቡናን ወደ ውጭ ስትልክ የኖረች ሀገር መሆኗን አስታውሰው፣ አሁን ለተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ዕድገት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።
ይህ ከፍተኛ ገቢ በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን ቡናን ከመትከል እና ከመንከባከብ ጀምሮ በመልቀም፣ በማጠብ፣ በማሸግ እና በማጓጓዝ ሂደት በተሠሩ የተቀናጁ ሥራዎች የተገኘ ውጤት መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ባለፉት ዐሥር ዓመታት ውስጥ በሀገር ውስጥ ያለው የቡና ፍጆታ (አጠቃቀም) በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሀገር ውስጥ ፍላጎት እያደገ ባለበት ሁኔታ ይህን ያህል የኤክስፖርት ገቢ ማሳካት መቻሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን አንሥተዋል።
ሀገራችን ይህንን ያላትን ሰፊ እምቅ አቅም ይበልጥ አጠናክራ መጠቀም እንዳለባትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: