ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ መንግሥት በትምህርት ዘርፍ እየሠራው ባለው ሥራ ከየትኛውም ዘርፍ በላይ እንደሚኮራ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው በአሁኑ ወቅት እጅግ የተሳካለት መሥሪያ ቤት ቢኖር ትምህርት ሚኒስቴር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህ ስኬትም የኢዜማ ፓርቲ አባል ቢሆኑም የትምህርት ፖሊሲውን በትክክል እየተገበሩ ለሚገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ምስጋና እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ድጋፍ በመለመን ጭምር ትምህርት ቤቶችን እንዳሠሩ እና መጻሕፍትን እንዳመጡ ጠቅሰው አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል።
መንግሥት ለቀጣዩ ትውልድ በማሰብ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ 35 ሺህ መዋዕለ ሕፃናትን መገንባቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤትም ከመደመር መጽሐፍ ሽያጭ እና ከሌሎች ምንጮች በተገኘ ገንዘብ 35 ሞዴል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ማስገንባቱን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት እየተሠሩ ያሉ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እና ዘመኑን የዋጁ መሆናቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ አሁን ላይ እየተገነቡ ያሉ ሞዴል አዳሪ ትምህርት ቤቶችም ውጤታቸው በቀጣይ በጉልህ የሚታይ መሆኑን አክለዋል።
በተማሪዎች ውጤት ላይ ስለሚታየው መቀነስ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የችግሩ መነሻ ከመሠረቱ ያልተሠራ ሥራ በመኖሩ መሆኑን አንስተዋል።
ይህንን ከመሰረቱ ለመለወጥ እና የትምህርት ሥርዓቱን ለማዘመን መንግሥት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) ዩኒቨርሲቲን ጭምር እየገነባ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ቀደም ሲል የነበረው የዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ታሳቢ የሚያደርገው ከግንባታው የሚገኘውን የኮንትራት ገንዘብ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን ግን ያንን አሠራር የሚቀይር ሥራ ተሠርቶ ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ኩረጃን ለማስቀረት እና ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በዚህም ተማሪዎች በራሳቸው አቅም ብቻ ጥረት አድርገው የማለፍ ባህል እየተፈጠረ መሆኑን ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል።
በለሚ ታደሰ