ዛሬ የተካሄደውን 6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ተከትሎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ጋር በመሆን በጋራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውነዋል።
ይህ መርሐ ግብር የሀገራችንን የፖለቲካ መሪዎች እና የሕዝብ ተወካዮችን በአንድ ዓላማ ያሰባሰበ ሲሆን፣ የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ይበልጥ የሚያጠናክር ሆኖ ተገኝቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት፣ “የፓርላማ ቆይታችንን ተከትሎ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውነናል፤ በዚህ የአረንጓዴ ዐሻራ ወቅት ተስፋን መትከላችንን እንቀጥላለን” በማለት የዕለቱን ውሎ በበጎ ዐሻራ ማጠናቀቃቸውን አመልክተዋል።
የዛሬው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የሕግ አውጪው አካል እና አስፈጻሚው አካል በሀገራዊ የልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስትራቴጂ ላይ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት ያሳየ ነው።
ምክር ቤቱ የሀገራችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ አስፈላጊ ውይይቶችን እና ውሳኔዎችን ካሳለፈ በኋላ፣ በቀጥታ ወደ መሬት ወርዶ ችግኝ መትከሉ መልዕክቱን የላቀ ያደርገዋል።
ዘንድሮ "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከችግኝ ተከላ ተግባር ባለፈ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ የምግብ ዋስትና፣ የአየር ንብረት መቋቋም እና የኢኮኖሚ ጥንካሬ መሠረት መጣሉን ለማሳየት ነው።
እያንዳንዷ የምትተከል ችግኝ የኢትዮጵያን የነገ ብሩህ ተስፋ የምታለመልም መሆኗንም ለማረጋገጥ ነው።
ይህ መርሐ ግብር መንግሥት ለአረንጓዴው ልማት የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ዜጋ በተሰማራበት የሥራ መስክ ሁሉ ለተፈጥሮና ለሀገር ዕድገት የድርሻውን እንዲወጣ የሚያነሳሳም ጭምር ነው።
በዚህ ወቅት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን በንቃት መደገፍና የተተከሉትን መንከባከብ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑንም የሚያስገነዝብ ነው።
በአድማሱ አራጋው