ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የሸቀጦች ወጪ ንግድ ገቢ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን አስታውቀዋል።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አፈጻጸም እና የወጪ ንግድ ገቢን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም፣ የዘንድሮው የኢትዮጵያ የሸቀጦች ወጪ ንግድ ገቢ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን ገልጸው፣ ይህም ከ1984 እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ በ17 ዓመታት ውስጥ ተመዝግቦ የነበረውን አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ በአንድ ዓመት ብቻ ማሳካት የተቻለበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመዋል።
ስኬቱ የግለሰብ ውጤት ሳይሆን፣ የሁሉም ዜጎች የጋራ ድል መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
መንግሥት በበጀት ዓመቱ ከወጪ ንግድ 9.8 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ከዕቅድ በላይ በማከናወን 11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አቅም ከዚህም በላይ ነው፤ የተገኘው ውጤት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ መስክ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን ዕድገት የሚያሳይ ነው ሲሉም አክለዋል።
በበጀት ዓመቱ ከአገልግሎት ዘርፍ 9.5 ቢሊዮን ዶላር፣ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ወደ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ፣ ከውጭ ምንዛሪ ልውውጥ ከ7 ቢሊዮን ዶላር በላይ፣ ከእርዳታ እና ብድር 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ መገኘቱንም ጠቅሰዋል።
በድምሩ በዘንድሮው በጀት ዓመት 38 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አመልክተዋል።
በሃና ምንዳሁን