ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም እና ብልጽግና ለማረጋገጥ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የፖለቲካ ተዋናዮች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች አቃፊ እና ይቅር ባይ ልብ እንዲኖራቸው ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ፣ ለኢትዮጵያ ሲባል በለውጡ መባቻ ላይ የነበረውን አቃፊነት ዳግም መተግበር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመሆኑም ታስረው ያሉትን ለመፍታት፣ በውጭ ሀገር የሚገኙትን እና በጫካ ውስጥ ትጥቅ አንስተው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በይቅርታ ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ ሰፊ ልብ ሊኖር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አንዳንድ ወገኖች በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆነው እንደሚናገሩ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ተስፋ እና የተሻለ ዕድል እንዳለ በተግባር በማሳየት አብሮ መሥራት እንደሚቻል ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
ሀገራዊ የምክክር መድረኩ የተሳካ እንዲሆን እና ኢትዮጵያ ሰላማዊ ሀገር እንድትሆን ልብን ማስፋት እና መተባበር ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
አያይዘውም ህወሓት አዕምሮውን ተጠቅሞ ቀልብ ከገዛ በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገር መንግሥት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው፣ ከሰላም ውጪ ያለው አማራጭ ለማንም እንደማይጠቅም እና የሀገራችን ቀዳሚ ፍላጎት ልማት እና ብልጽግና መሆኑን አስገንዝበዋል።
ለዚህ ስኬትም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ አድርገዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤት ውስጥ ሀገራቸውን ያገለገሉ የብልጽግናም ሆነ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ላበረከቱት አስተዋጽኦ በጀግንነት መስለው አመስግነዋል።
በተለይም የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ያሳዩትን ቁርጠኝነት፣ ሐሳባቸውን በግልጽ የመግለጽ ድፍረት እና ያራመዱትን የበሰለ የፖለቲካ ባህል በከፍተኛ ደረጃ አድንቀዋል።
የትብብር መስኩ በፓርላማ ቆይታ ብቻ የተወሰነ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ሁሉም አካላት ልባቸውን አቅንተው በጋራ እንዲሠሩ፣ በተለይም አሁን ላይ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ባለው የኮሪደር ልማት ሥራዎች ላይ በጋራ እንዲሰለፉ አደራ ብለዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ