በሃገር አቀፍ ደረጃ ከ25 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የ2018 ዓ.ም ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር በሐዋሳ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።
ይህ ሰፊ ሀገራዊ መርሃ ግብር ወጣቶች በመላ ኢትዮጵያ በ14 የተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘርፎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ፣ ለህብረተሰቡ ዘርፈ-ብዙ አገልግሎት የሚሰጡበት መድረክ ነው።
የሲዳማ ክልል ርዕስ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ እና የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በተገኙበት መርሃ ግብሩ ተጀምሯል።
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከአላማው አንፃር አዎንታዊ ውጤት እየተመዘገበበት ይገኛል ብለዋል።
በተለያዩ የበጎ ፍቃድ ተግባራት ላይ ወጣቱ ነፃ አገልግሎት በመስጠት በከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ሊሰሩ የሚችሉ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።
አምስተኛ ዙር ላይ የደረሰው ወስን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ፣ወጣቶች የኢትዮጵያን መልክ እና የማህበረሰብ እሴቶችን እንዲያውቁ ትልቅ እድል ለመፍጠር ማስቻሉን አመልክተዋል ።
ርዕስ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ወጣቶች በሚሰማሩበት አከባቢ ሁሉ ቤተሰባዊነትን በማጠናከር አብሮነትን ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
በዚህ በ5ኛው ዙር ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ53 ሚሊየን በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል።
በሚካኤል ገዙ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: