Search

በአዲስ አበባ የቤት ኪራይ ጭማሪ ጣሪያ 11.5% ሆኖ ተወሰነ፤ የውል እድሳት ምዝገባም ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል

ረቡዕ ሐምሌ 01, 2018 373

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኪራይ ገበያው ላይ የሚስተዋለውን ህገ-ወጥ እና የዘፈቀደ የዋጋ ጭማሪ በዘላቂነት ለመግታት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ ወስዷል።

ከዚህ ቀደም በወጣው የቤት ኪራይ ቁጥጥር አዋጅ መሠረት፣ ለ2019 በጀት ዓመት የሚተገበረው ፍትሐዊ የቤት ኪራይ ዓመታዊ ጭማሪ ጣሪያ 11.5 በመቶ ብቻ ሆኖ መጽደቁን የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በይፋ አስታውቋል።

ይህንን ውሳኔ ተከትሎ በከተማዋ የሚገኙ የግል መኖሪያ ቤቶች የአከራይ እና ተከራይ አዲስ የውል እድሳት ምዝገባ ከዛሬ ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክፍለ ከተማ የቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች በመተግበር ላይ ይገኛል።

የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እንዳብራራው ይህ የዋጋ ማስተካከያ ጣሪያ በዘፈቀደ የተደረገ ሳይሆን፣ በከተማዋ ሰፊ ሳይንሳዊ ጥናት ተካሂዶ የነዋሪውን እውነተኛ የመክፈል አቅም እና የኢኮኖሚ ሁኔታውን ባገናዘበ መልኩ የተዘጋጀ ነው።

ይህ አዲሱ አሰራር አከራዮች ወቅቱን ያገናዘበ ፍትሐዊ ገቢ እንዲያገኙ የሚያረጋግጥ ሲሆን፤ በተጓዳኝ ደግሞ ተከራዮች ከገቢያቸው ጋር የተመጣጠነ ኪራይ በመክፈል ከተደጋጋሚ መፈናቀል እና ከስነ-ልቦና ስጋት ድነው የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ይህ ውሳኔ በከተማዋ ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ረገድ የጎላ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የመልካም አስተዳደር ፋይዳዎች እንዳሉት ተረጋግጧል።

የአከራይ እና ተከራይ ግንኙነትን በሕግ ማዕቀፍ በመምራት የሁሉንም ወገን የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተችሏል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: