Search

የመግባባት ዴሞክራሲን ያፀናው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ

ረቡዕ ሐምሌ 01, 2018 108

ዴሞክራሲን በማስፈንና በተለይ በሀገራችን ለዘመናት የቆዩና የተካረሩ የፖለቲካ ልዩነቶችን በማረቅ፣ የጥላቻን ግድግዳ አፍርሶ የትብብርን ድልድይ ለመገንባት "የመግባባት ዴሞክራሲ"  ወደር የለሽና ፍቱን አማራጭ መሆኑን በብዙ ምክንያቶች ማረጋገጥ ይቻላል።

መንግሥት በብዝኃነት በደመቀችና የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎት ባለባት ሀገራችን፣ አሸናፊው ሁሉንም በሚወስድበት የፉክክርና የዜሮ ድምር ፖለቲካ ብቻ መጓዝ ሀገርን እስከመበተን ሊያደርስ የሚችል አደጋ አለው ብሎ በፅኑ ያምናል። በመሆኑም፣ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታትና አቃፊ የሆነ ሥርዓት በመገንባት፣ የጋራ ቤታችንን ለማጽናት የመግባባት ዴሞክራሲ ዋነኛ የመንግሥት የፖለቲካ ማዕቀፍ ከሆነ ከራርሟል።

የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ በሚቀይርና ሥር ነቀል የባህል ሽግግር በሚያመጣ መልኩ፣ መንግሥት ይህንን የመግባባት ዴሞክራሲ ዕውን ለማድረግ ድፍረት የተሞላባቸውንና ያልተለመዱ ታሪካዊ እርምጃዎችን ወስዷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ይህንኑ የዴሞክራሲ ቁርጠኝነት በተግባር አሳይተዋል።

መንግሥት ለዴሞክራሲ ቀናኢነት ሲል በምርጫው 15 በመቶውን ወንበር ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲወዳደሩበት በመተው፣ በ85 በመቶው ላይ ብቻ ለመወዳደር መወሰኑ በድፍን አፍሪካ ታይቶ የማይታወቅ ታሪካዊ ክንውን መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። በተጨማሪም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተፎካካሪ ፓርቲ ተወክለው በእውቀታቸውና በአቅማቸው ሀገራቸውን ላገለገሉ የኢዜማ፣ የአብን፣ ሌሎችም የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትና የግል ተወዳዳሪዎች በምክር ቤቱ የሕዝብ ጥያቄን በማንሳታቸው ከፍ ያለ ምስጋና ማቅረባቸው፣ መንግሥት ለተፎካካሪዎች ያለውን ጥልቅ አክብሮት ያሳያል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ውስጥ የመግባባት ዴሞክራሲ መለያ የሆኑ አንኳር ሀሳቦችን አንጥሮ ማውጣት ይቻላል። የመጀመሪያውና ትልቁ መለያ አካታችነትና የሥልጣን ክፍፍል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው "መንግስታችን እናንተን አካቶ ኢትዮጵያን ማልማት ይፈልጋል፤ ኢትዮጵያ የጋራ ሀገራችን ናት... በምክር ቤት ብቻ ሳይሆን በተለያየ ዘርፍ ተባብረን ኢትዮጵያ እንድናበለጽግ አብረን እንድንሰራ ጥሪ ላቀርብላችሁ እፈልጋለሁ" በማለት ተፎካካሪዎችን በሀገር አስተዳደር ውስጥ ማሳተፍ የመንግሥት ጽኑ ምኞት መሆኑን አስገንዝበዋል። ሁለተኛው መለያ ለብሔራዊ መግባባት የተፈጠረው ምህዳር ነው። ታፍነው የቆዩ ታሪካዊ ችግሮችን ለመፍታት በመንግሥት አነሳሽነት "አካታች ሀገራዊ ምክክር" (Inclusive National Dialogue) መጀመሩና፣ በስልጣን ላይ ያለ መንግስት  ከ2 የሥልጣን ዘመን (ተርም) በላይ መቆየት የለበትም የሚል አጀንዳ ቀርቦ በመንግሥት በኩል ቁርጠኝነት መወሰዱ ዴሞክራሲን ሥር ለማስያዝ የተወሰደ ጉልህ የመግባባት ዴሞክራሲ እርምጃ ነው።

አብላጫ ድምፅና ሥልጣን ያለው መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ሲል በገዛ ፈቃዱ ወንበርን ለተፎካካሪዎች አሳልፎ የሚሰጥበት አሰራር በዓለም ላይ እጅግ ጥቂት ሀገራት ብቻ የሞከሩት ድንቅ ተሞክሮ ነው። እንደ ደቡብ አፍሪካው ከአፓርታይድ ማብቃት በኋላ የተቋቋመው የብሔራዊ አንድነት መንግሥት፣ ወይም እንደ ስዊዘርላንድ የካቢኔ ሥልጣንን አከፋፍሎ አብሮ የመምራት አካታች አሰራሮችን የኢትዮጵያ መንግሥት ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣምና የጋራ ብልጽግናን በማለም እያተገበራቸው ይገኛል።

በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማው "የሚያስፈልገን ሰላም ነው፣ ትብብር ነው፣ አብረን መስራት ነው" በማለት ያቀረቡት የፍቅርና የአብሮነት ጥሪ፣ መንግሥት ሀገራችንን ከዜሮ ድምር የመጠፋፋት ፖለቲካ አውጥቶ ወደ ስልጡን የመግባባት ዴሞክራሲ እያሸጋገራት መሆኑን ያረጋግጣል። ይህ የዴሞክራሲ ምህዳርን የማሳደግና መግባባት የሰፈነባት ሀገር የማድረግ የመንግሥት ጥረት በብዙ ሀገራት ያልተለመደ ቢሆንም፣ ልዩነትን አቻችሎና አቅሞችን ደምሮ ኢትዮጵያን ጠንካራ፣ አካታችና የሁላችንም የምትሆን የጋራ ቤት ለማድረግ አዲስ ብሩህ የፖለቲካ ንጋት አብስሯል።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ