በግንባታው ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ ያለው ፍሬድ ሚልስ ከ4 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች በላይ ባሉት ዩቲዩብ ቻናሉ ላይ “አውሮፕላን ማረፊያው አፍሪካን ይቀይራል” በሚል ርዕስ ኢትዮጵያ በቢሾፍቱ እየገነባች ስላለው ግዙፍ ፕሮጀክት አስገራሚ ትንታኔ አቅርቧል፡፡
ፍሬድ ሚልስ በዩናይትድ ኪንግደም የግንባታ ዘርፍ የቀድሞ የንድፍ ሥራ አስኪያጅ እና ከ4 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት “The B1M” የተሰኘ ዩቲዩብ ቻናል ባለቤት ነው፡፡
12.5 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጀው ይህ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ትልቁ የአቪዬሽን ፕሮጀክት መሆኑን ሚልስ ያነሳል፡፡
እንደ ሚልስ አባባል የፕሮጀክቱ ልዩነት የመንገደኞች መግቢያ እና መውጫነቱ ብቻ ሳይሆን ሆቴሎችን፣ የንግድ ማዕከላትን፣ ቢሮዎችን እና የጭነት ማስተናገጃዎችን ያካተተ የተሟላ የአቪየሽን ከተማ መሆኑ ላይ ነው፡፡
በዓለም አቀፉ የዛሃ ሃዲድ አርክቴክቶች የተሠራው የሕንጻው ንድፍ የኢትዮጵያን መልክዓ ምድር ባህል እና አየር ንብረት ያማከለ ነው ይላል ባለሙያው፡፡
በተለይም ተሳፋሪዎች ከአንዱ በር ወደ ሌላኛው የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማሳጠር የታሰበው ማዕከላዊ መስመር ታላቁን የስምጥ ሸለቆ የሚወክል እንደሆነ ይገልጻል፡፡
ይህ ሜጋ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከዓለማችን ታላላቅ አውሮፕላን ማረፊያዎች ጋር ሲነጻጸር አስገራሚ ብልጫ ይኖረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዓመት ከ20 እስከ 30 ሚሊዮን መንገደኞችን ከሚያስተናግዱት እንደ ካይሮ እና ኦ.አር ታምቦ ካሉ የአፍሪካ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች በእጅጉ እንደሚልቅ አንስቷል፡፡
አዲሱ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ፣ በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማስተናገድ እየተገነባ ይገኛል፡፡
ይህ አሃዝ በዓለም ላይ በግዙፍነታቸው ከሚታወቁት የለንደኑ ሂትሮው፣ የቱርኩ ኢስታንቡል፣ የዱባይ እና የአሜሪካው ሃርትስፊልድ-ጃክሰን አውሮፕላን ማረፊያዎች በብዙ ሚሊዮኖች የሚበልጥ እንደሆነም ይጠቅሳል፡፡
ይህም የቢሾፍቱን አውሮፕላን ማረፊያ በታሪክ አይተነው የማናውቀውን እጅግ በርካታ ተሳፋሪዎችን የሚያስተናግድ ማዕከል ያደርገዋል እንደ ሚልስ ትንታኔ፡፡
የቦታው ስፋትም 35 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ጠቅሶ፣ 12 ካሬ ኪሎ ሜትር ከሆነው የሂትሮው እና 21 ካሬ ኪሎ ሜትር ከሆነው የጄኤፍኬ (JFK) ማረፊያዎች በእጥፍ የሰፋ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ካርጎው በዓመት 4 ሚሊዮን ቶን ጭነት የማስተናገድ አቅም የሚኖረው ሲሆን፣ በዓለም ላይ ካሉ አምስት ዋና ዋና የካርጎ ማስተናገጃ ማዕከላት ተርታ ያሰልፈዋል፡፡
የአፍሪካ የአቪዬሽን ገበያ በዓለም ላይ በፍጥነት በማደግ ላይ መሆኑን በማውሳት፣ እ.አ.አ ከግንቦት 2025 እስከ ግንቦት 2026 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ የአህጉሪቱ የአየር መንገድ አቅም በ6.7 በመቶ ወይም በ24 ሚሊዮን ወንበሮች ማደጉን ይጠቅሳል፡፡
ይህ አሀዝ በዚሁ ተመሳሳይ ወቅት 1.7 በመቶ ዕድገት ካሳየው የደቡብ ምሥራቅ እስያ፣ 2 በመቶ ዕድገት ካስመዘገበው አውሮፓ እና 1 በመቶ ብቻ ከሆነው የዓለም አማካይ ዕድገት ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
አፍሪካ ቀጥታ በረራ ያላቸው መስመሮች 19 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ አህጉሪቱ የራሷ የሆነ አንድ ግዙፍ ማዕከል የላትም፡፡
ኢትዮጵያ ይህን አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ መገንባቷ በፍጥነት እያደገ ካለው ከዚህ የአፍሪካ ገበያ ከፍተኛውን ድርሻ እንድትወስድ ያስችላታል፡፡
ከሚስተናገዱት መንገደኞች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት አውሮፕላን ማረፊያውን እንደ መሸጋገሪያ በመጠቀም በሌላ አውሮፕላን ጉዟቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡
በዚህም መሰረት ቢሾፍቱ አፍሪካን ከእስያ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከአውሮፓ ጋር የሚያገናኝ ግዙፍ ዓለም አቀፍ የጉዞ ማዕከል ትሆናለች፡፡
ለዚህ ግዙፍ ስኬት የቦታው ምርጫም ልዩ አቅም ፈጥሮለታል፡፡ ቢሾፍቱ ከአዲስ አበባ በ35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ የቦታው ከፍታም ከአዲስ አበባ በ400 ሜትር ዝቅ ብሎ በ1ሺህ 900 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ዝቅተኛ ከፍታ አየሩ ጥቅጥቅ ያለ እንዲሆን በማድረግ የአውሮፕላን ሞተሮች ብዙ አየር ስበው ከፍተኛ ግፊት እንዲፈጥሩ እና ክንፎችም የተሻለ የማንሳት አቅም እንዲኖራቸው እንደሚረዳ ባለሙያው ይጠቅሳል፡፡
በመሆኑም ከዚህ የሚነሱ አውሮፕላኖች አነስተኛ ነዳጅ ተጠቅመው ረጅም ርቀት መጓዝ ስለሚችሉ ፕሮጀክቱ ከዓለም ዙሪያ ለሚመጡ በረራዎች ተመራጭ ያደርገዋል፡፡
አውሮፕላን ማረፊያው የዓለማችንን ግዙፍ አውሮፕላኖች ማስተናገድ የሚችሉ አራት (Code 4E) የመንደርደሪያ መንገዶችን አካትቷል፡፡
ፕሮጀክት ከ50 በላይ ሀገራት የተፈራረሙትን የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን (AfCFTA) በከፍተኛ ደረጃ የሚደግፍ እና ኢትዮጵያ በአቪዬሽኑ ዘርፍ ያላትን የመሪነት ሚና ይበልጥ የሚያጠናክር ታሪካዊ ክንውን እንደሆነ ጠቅሷል ሚልስ፡፡
በለሚ ታደሰ