የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጥንካሬ እና ሉዓላዊነት ምንጊዜም ከቀይ ባሕር ጠረፍ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው።
ከጥንቱ የአክሱም ሥልጣኔ እስከ ዘመናዊው የታሪክ ምዕራፍ ድረስ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ጉልህ አሻራ ነበራት።
በታላቁ የአዱሊስ ወደብ አማካኝነት የሕንድ ውቅያኖስን እና የሜዲትራኒያንን የንግድ መስመሮች በመቆጣጠር፣ የራሷን ሳንቲም በማተም እና ጠንካራ የባሕር ኃይል በማሰማራት ከታላላቅ የዓለም ኃያላን ተርታ ተሰልፋ እንደነበር ታሪክ የማይክደው ሀቅ ነው።
ቀዳማዊ አፄ ዓምደጽዮን እና አፄ ዘርዓ ያዕቆብን የመሳሰሉ ነገሥታት የቀይ ባሕርን ጠረፍ እና የዘይላን የንግድ ኮሪደር ለመጠበቅ ከፍተኛ መዋቅሮችን ዘርግተው ነበር።
በዘመናዊቷ ኢትዮጵያም ቢሆን በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የተመሠረተው የባሕር ኃይል በቀይ ባሕር አካባቢ ያለውን የጸጥታ ሚዛን ለመጠበቅ ሙሉ አቅም ነበረው።
ታሪካዊ አሻጥሮች እና ኢትዮጵያን ከባሕር የማራቅ ሤራ
ይህ የተፈጥሮ እና የታሪክ ባለቤትነት ግን በውጭ ኃይሎች ሤራ በተደጋጋሚ ሲደናቀፍ ቆይቷል።
እ.አ.አ ሰኔ 3 ቀን 1884 በእንግሊዝ መንግሥት እና በአፄ ዮሐንስ 4ኛ መካከል የተፈረመው የሂውት ውል (Hewett Treaty) ለዚህ ሤራ ዋነኛ ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ በሱዳን የተከበቡ የግብፅ ወታደሮችን በሰላም ለማስወጣት ቃሏን ብትጠብቅም፣ እንግሊዝ ግን ምፅዋን ለጣልያኖች አሳልፋ ሰጠች።
በሌላ በኩል ደግሞ የሱዳን መህዲስቶችን በማነሳሳት አፄ ዮሐንስ 4ኛ በመተማ በኩል በሁለት ግንባር እንዲወጠሩ የጂኦፖለቲካ ሤራ ተጠነሰሰ።
በ1928 ዓ.ም ፋሺስት ጣሊያን ሀገራችንን ስትወርር ጅቡቲን ትቆጣጠር የነበረችው ፈረንሳይ ኢትዮጵያ በሕጋዊ መንገድ የገዛቻቸው የጦር መሣሪያዎች ወደ መሃል አገር እንዳይገቡ ማገዷ አይዘነጋም።
ይህም ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሲቀነባበር የኖረው ሤራ የኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር መራቅ ለደኅንነቷ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ በግልፅ ያሳየ ነበር።
የምፅዋ ሰቆቃ እና የትውልዱ የደም መስዋዕትነት
የኢትዮጵያ ልጆች የባሕር በራቸውን ለማስጠበቅ የከፈሉት የደም ዋጋ መቼም አይረሳም። የካቲት 1982 ዓ.ም በምፅዋ ወደብ የተካሄደው ውጊያ በታሪካችን እጅግ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከተከፈለባቸው አውደ ውጊያዎች አንዱ ነው።
ለአሥር ቀናት ያለማቋረጥ በተካሄደው መራራ ፍልሚያ ከ9 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች ተሰውተዋል።
የ6ኛ ነበልባል ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ተሾመ ተሰማ እና የ3ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ በጠላት እጅ ላለመማረክ የኢትዮጵያን ባንዲራ ለብሰው ሕይወታቸውን የሰጡበት ቆራጥ ውሳኔ የዚህ እውነት የዘለዓለም ምስክር ነው።
የዛሬው ትውልድ መብቱን ሲጠይቅ፣ ያን አጥንቱን የዘራበትን እና ደሙን ያፈሰሰበትን ታሪክ እያስታወሰ ነው።
የኢትዮጵያ ጥያቄ፡ ከቀጣናዊ ሰላም እስከ ዓለም አቀፍ ትስስር
ዛሬ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የታሪክ ብቻ ሳይሆን የነባራዊ እውነታ እና የህልውና ጥያቄ ነው።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት፣ በፍጥነት እያደገች ያለች እና የ 'BRICS' አባል የሆነች ሀገር ወደብ አልባ ሆና መቆየቷ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፉ የንግድ ሰንሰለትም ማነቆ ነው።
ባሕሩ መቶ ኪሎ ሜትር እንኳን በማይሞላ ቅርበት እያለ በየዓመቱ ከ1.5 አስከ 2 ቢሊዮን ዶላር የወደብ ኪራይ መክፈል ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን በእጅጉ የሚገታ ነው።
የኢትዮጵያ ጥያቄ ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለ እና በተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ስምምነት (UNCLOS) አንቀጽ 125 እና 127 መሠረት ወደብ አልባ ሀገራት ያላቸውን የትራንዚት እና የጋራ ተጠቃሚነት መብት የተመረኮዘ ነው።
ቀይ ባሕር የዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት እና የውጭ ሀገራት የጦር ሠፈር መናኸሪያ በሆነበት በዚህ ዘመን ጠንካራ አቅም ያላት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ንቁ ተሳትፎ ቢኖራት ቀጣናዊ ሰላም ይበልጥ አስተማማኝ ይሆናል።
የትውልዱ የቤት ሥራ
በመሆኑም ይህ የመልክዓ ምድር እስር ቤት ሊሰበር የሚገባው አሁን ነው። ይህ ጉዳይ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የእያንዳንዱ ዜጋ የህልውና ጥያቄ ነው።
የአሁኑ ትውልድ ይህንን እና መሰል ታሪካዊ እውነታዎችን በጥልቀት በማንበብ፣ ተቋማዊ በሆኑ ጥናቶች በመታገዝ እና ዲጂታል አውታሮችን በመጠቀም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድምጹን በምክንያታዊነት ሊያሰማ ይገባል።
ሁሉም ዜጋ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የኢትዮጵያን ትክክለኛ የባሕር በር እና የጋራ ተጠቃሚነት ጥያቄ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች በማስረዳት የዲጂታል ዲፕሎማሲ ድርሻውን መወጣት አለበት።
የባሕር በር ጥያቄ የብሔራዊ ደኅንነት እና የኢኮኖሚ ትንሣኤያችን ቁልፍ መሆኑን ተረድተን፣ ከልዩነቶቻችን በላይ ለሀገር ጥቅምና ለጋራ ብልጽግና በአንድ ድምፅ መቆም ወሳኝ ጉዳይ ነው።
መጻኢው ጊዜ የፍትሐዊነት እና የቀጣናዊ ትስስር መድረክ እንዲሆን የሀገራችንን ሉዓላዊ መብት ለማስከበር በጋራ መሥራት ጊዜ የማይሰጠው አገራዊ ጥሪ ነው፡፡
በለሚ ታደሰ